የአማራ ልዩ ኃይልና ፖሊስ “አታስፈልግም” ተብሎ እንደነበር የክልሉ ኮሚሽነር አበረ ገለጹ
የአማራ ልዩ ኃይል፣ፖሊስ፣ሚሊሻና ሌሎች የጸጥታ አካላት የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ከማስበርም ባለፈ ሀገራዊ አንድነት በሚያስጠብቅ መልኩ የተዋቀረ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አስታወቁ፡፡
የክሌሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ለአማራ ቴቪ እንደገለጹት የክልሉ ልዩ ኃይልና ፖሊስ አታስፈልግም ተብሎ የተገፋ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ ክልሉ በአጠቃላይ የጸጥታ ኃይል እንዲኖረው አይፈልግም ነበር ያሉት ኮሚሽነሩ ልዩ ኃይሉና ሚሊሻው ግን በግንባር ተሰልፎ ተጋድሎ ሲፈጽም ነበር ብለዋል፡፡ የክልሉ ሕዝብና ሌሎች የጸጥታ አካላት የክልሉን የውስጥ ሰላም በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ኃላፊነት እየተወጡ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የክልሉ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር ተሰልፎ በሀገርንና ሕዝብ ላይ ችግር የሚፈጥሩ አካላትን በመዋጋት አስመስክሯል ብለዋል፡፡ ልዩ ኃይሉና ፖሊስ የተገፋና ዋጋ የለህም ተብሎ የነበረ፤አንገቱን እንዲደፋም የተደረገ ነበር ሲሉ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡ የጸጥታ ኃይል ለሕዝብ ምልክትና መከበሪያ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ የአማራ ሕዝብ ግን ይህ የጸጥታ አካል እንዳኖረው ሲደረግ ነበር ብለዋል፡፡ “የአማራ ልዩ ኃይል ተባልን እንጅ የኢትዮጵያ ልጆች ነን፤ ይዘታችንም ኢትዮጵያዊ ነው “ ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (ትህነግ) ከዋጃ ጀምሮ እስከ ሁመራ ያደርጋቸው በነበሩ እቅስቃሴዎች ምን ሊያደርግ እንደሚችል ከ6 ወር በፊት እናውቅ ነበር የሚሉት ኮሚሽነር አበረ ትህነግ በተጨባጭ ውጊያ እንደሚገጥም እናውቅ ነበር ብለዋል፡፡ ይንንም በነበረው ትጥቅ፣አደረጃጀት ማወቅ መቻሉንና መጀመሪያ ኃይሉን በብርጌድ ማዋቀሩን መረጃ ደርሶን ነበር ብለዋል፡፡
ይሁንና ቡድኑ በኋላ ኃይሉን ወደ ክፍለ ጦር ብሎም ሜካናይዝድ ማደራጀትና ልዩ ኮማንዶ ማዘጋጀት ጀመሮ እንደነበር አንስተዋል፡፡ ይህንን ሲያደርግ “እናውቅ ነበር “ ያሉት ኮሚሽነሩ “እኛም ራሳችንን ስናደራጅ ነበር “ ብለዋል፡፡ አጠቃላይ የአማራ ሕዝብ ለሀገሩ ወታደር ሆኖ ሀገሩን ተከላክሏል ብለዋል፡፡
የምንታገሰው ጥቂቶች ባጠፉት ሀገር እንዳይፈርስ መጥፎ ታሪክ እንዳይሰራ እንጅ መተከል ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍ ከጠመንጃም በላይ ካለ እንዲነሳ ያስገድዳል ብለዋል፡፡
“ነፍሰ ጡር ሴት ሆዷ ተቀዶ ህፃኑ ወጦ የተበላበት ፥ ሰው በቀስት ሆዱን ተመቶ አንጀቱ ተጎልጉሎ እዲወጣ የተደረገበት በምድር ላይ ከመተከል ውጭ የትም አልተፈፀመም “ ብለዋል፡፡ ይህንን ለፌዴራል መንግስት እያመለከትን ነው ያሉት ኮሚሽር አበረ፤ ወይ ኃላፊነት ስጡን እንግባና የሕዝባችንን ሰላም እናስከከበር ወይ ራሳችሁ አስከብሩ ብለን ለፌዴራል መንግስት ገልጸናል ብለዋል፡፡ “ያንን አካባቢ ማነው ለተወሰኑ ሰዎች የሰጠው፤ የኢትዮጵያ መሬት እኮ ነው፤ ማንም ሰው እዛ ቦታ ላይ ሄዶ መኖር ይችላል መብቱ ነው ይህንን የሚከለክል ካለ ደግሞ እስከ መጨረሻው እንዋጋዋለን ከዚህ በኋላ አንታገስም “ ብለዋል፡፡