ንግድ ባንክ በሲስተም ችግር ምክንያት ምን ያክል ገንዘብ አጣ፤ ምን ያክልስ አስመለሰʔ
ባንኩ በገጠመችው ችግር ሊያጣው ከነበረው 800 ሚሊየን ብር እስካሁን 623 ሚሊየኑን ማስመለስ መቻሉን አስታውቋል
ከባንኩ በህገወጥ መንገድ 9.8 ሚሊየን ብር ወስደው የጠፉ 567 ሰዎችም እየተፈለጉ ነው ተብሏል
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባሳለፍነው ሳምንት አርብ እለት ያጋጠመውን የሲስተም ችግር አስመልክቶ እያደረገ ያለው ስራ የደረሰበት ደረጃ ላይ መግለጫ ሰጥቷል።
የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ በሰጡት መግለጫ፤ ችግሩ የት ጋር ነው ያጋጠመው የሚለው ላይ በባለሙያ ጥናት እየተደረገ ነው ገና አላለቀም ብለዋል።
በእለቱ በተፈጠረው የሲስተም ችግር ጋር ተያይዞ በተደረጉ ግብይች እና የገንዘብ ዝውወሮች ዙሪያም ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በእለቱ ሊጠፋ የነበረ ወይም አንድ ሰው ገንዘብ ከአካውንቱ ገንዘብ ካስተላለፈ በኋላ ለተላከለትም ሰው ደርሶ ገንዘቡ ለላኪውም ተመለሶ የተተካ ወይም ሪቨርስ ያደረገ 801 ሚሊየን 417 ሺህ 800 ብር ነበር ብለዋል።
በእለቱ አጋጥሞ በነበረ የሲስተም ችግር በነበረበት መስመር ላይ 25 ሺህ 761 ደንበኞች ግብይት ፈጽመዋል ያሉት ፕሬዝዳቱ፤ በዚሁ ሰዓት 238 ሺ 293 ጊዜ ግብይት መፈጸሙን አብራርተዋል።
ባለፈው 490 ሺህ ግብይት ተፈጽሞ እንደነበረ ማሳወቃቸውን ያስታወሱት አቶ አቤ ሳኖ፤ ችግር ባለበት መስመር የተፈጸመው ግብይት 238 ሺ 293 እንደነበረ እና ሌሎቹ ግብይቶች ችግር ባልነበረበት መስመር የተከናወኑ መሆናቸው አስታውቀዋል።
በእለቱ ተገቢ ያልሆነ ግብይት ወይም የገንዘብ ዝውውር የተፈጸመባቸው አካውንቶች 25 ሺህ 671 እንደነበሩ በመጥቀስም አንድ ደንበኛ በአማካይ ከ9 ጊዜ በላይ ግብይት መፈጸሙን ነው በመግለጫቸው ያነሱት።
በእለቱ አንድ ወይም ሁለት ግብይት የፈጸሙ ደንበኞች ጥርጣሬ ውስጥ እንዳልገቡ እና ያለ አግባብ የተወሰደ ገንዘብ ከሂሳባቸው ተቀናሽ ተደርጎ እንደሚመለስ መደረጉንም አስታውቀዋል።
በዚህም በአካውንታቸው ላይ በቂ ገንዘብ ከነበራቸው 10 ሺህ ደንበኞች ላይ 44 ሚሊየን ብር ተመላሽ መደረጉን ነው የባንኩ ፕሬዝዳንት የገለጹት።
ቀሪዎቹ 15 ሺሀ 8 ደንበኞች 207 ሺህ ግብይት ፈጽመዋል ያሉት አቶ አቤ፤ ይህም እያንዳንዱ በዚያ ሌሊት በአማካይ 14 ጊዜ ግብይት መፈጸሙን ያሳያል ብለዋል።
ሂሳባቸው ላይ ካለው ብር ወስደው ከነበሩ 15 ሺሀ 8 ደንበኞች መካከል እስከ ትናንት ማታ ድረስ 372 ሚሊየን ብር ድረስ ተመላሽ መደረጉንም አስታውቀዋል።
ከእነዚህ ውስጥ 9 ሺህ 281 ሰዎች ሙሉ በሙሉ ያለባቸውን መክፈላቸውን እንዲሁም 5 ሸህ 160 በከፊል መልሰው ቀሪውን ለመክፈል ቃል መግባታቸውን ነው አቶ አቤ በመግለጫቸው ያብራሩት።
በዚህም መሰረት እስካሁን በድምሩ ሊጠፋ ከነበረው 800 ሚሊየን ብር ውስጥ 623 ሚሊየን ብር መሰብሰቡን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ ቀሪውን የማስመለስ እና የማፈላለግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በህገ ወጥ መንገድ ገንዘብ ከወሰዱት መካከል 567 ደንበኞች ጠፍተዋል ያሉት ፕሬዝዳቱ፤ ሙሉ አድራሻውን አለን፤ እየፈለግናቸው ነው ብለዋል።
እነዚህ የጠፉ ደንበኞች የወሰዱት ገንዘብ 9.8 ሚሊየን ብር መሆኑን እና ከዚህም ውስጥ አንድ ሰው ያወጣው ትልቁ ገንዘብ 324 ሺህ ብር መሆኑንም ገልጸዋል።
በተሰጣቸው እድል ገንዘብ ባልመለሱ ደንበኞች ላይ በቀጣይ ስለሚወሰድ እርምጃ በሰጡት ማብራሪያም፤
በባንኩ ቅርንጫፎች በያሉበት ስም ዝርዝራቸውን መለጠፍ እንዲሁም በባንኩ የማበራዊ ትስስር ገጾች ስማቸውን ማውጣት አንዱ ነው ብለዋል።
2ኛ እርምጃ ስማቸውን ከነፎቶዋቸው ጭምር በማውጣት ማሳወቅ ሲሆን በዚህም መመለስ ካልቻሉ 3ኛ እርምጃ በህግ የመጠየቅ ይሆናል ብለዋል።
ባንኩ ያለአግባብ የተወሰደ ገንዘቡን አንድ ብር እንኳ ሳይቀር እንደሚያስመልስም አቶ አቤ ቃል ገብተዋል።