ከንግድ ባንክ የራሳቸው ያልሆነ ገንዘብ ያንቀሳቀሱ ግለሰቦች የማይመልሱ ከሆነ በህግ እንደሚጠየቁ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፈው ሳምንት አርብ እለት "የሲስተም ችግር" ባጋጠመው ወቅት ደንበኞች የራሳቸው ያልሆነ ገንዘብ ወጭ ማድረጋቸውን እና ማዘዋወራቸውን መግለጹ ይታወሳል
ፋይናንስ ኢንተሊጀንስ አገልግሎቱ የራስ ያልሆነን ገንዘብ ህጋዊ ማድረግ እንደ ወንጀሉ ክብደት እስከ 25 የሚዘልቅ እስራት ያስቀጣል ብሏል
ከንግድ ባንክ የራሳቸው ያልሆነ ገንዘብ ያንቀሳቀሱ ግለሰቦች የማይመልሱ ከሆነ በህግ እንደሚጠየቁ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ
ግዙፉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያጋጠመውን ችግር ተከትሎ የራሳቸው ያልሆነ ገንዘብ ውጭ ያደረጉ ወይም ያዘዋወሩ ግለሰቦች ገንዘቡን የማይመልሱ ከሆነ በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዛሬ ባውጣው መግለጫ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፈው ሳምንት አርብ እለት "የሲስተም ችግር" ባጋጠመው ወቅት ደንበኞች የዲጂታል ባንኪንግ ሲስተሙን ተጠቅመው የራሳቸው ያልሆነ ገንዘብ ወጭ ማድረጋቸውን እና ማዘዋወራቸውን መግለጹ ይታወሳል።
በተፈጠረው ችግር ዙሪያ ከባንኩ ጋር በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ የገለጸው ፋይናንስ ኢንተሊጀንስ አገልግሎቱ የራስ ያልሆነን ገንዘብ ህጋዊ ማድረግ እንደ ወንጀሉ ክብደት እስከ 25 የሚዘልቅ እስራት ያስቀጣል ብሏል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ያራሳቸው ያልሆነ ገንዘብ ያወጡ ግለሰቦች መኖራቸውን ገልጾ፣ ገንዘቡን እንዲመልሱ ጠይቆ ነበር።
ተማሪያዎች የራሳቸው ያልሆነ ገንዘብ አውጥተዋል ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችም "ተማሪዎች ገንዘብ መልሱ" የሚል ማስታወቂያ በየግቢያቸው ለጥፈው ታይተዋል።
ባንኩ ችግር በተፈጠረበት ወቅት ጤናማ የሆኑትን ጨምሮ 490ሺ የገንዘብ ዝውውሮች መፈጸማቸውን የባንኩ ፕሬዝደንት አቤ ሳኖ የተፈጠረውን "የሲስተም ቸግር" አስመልክተው ከሁለት ቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
ፕሬዝደንቱ እንዳሉት ችግር በተፈጠረበት ወቅት ዝውውር የተፈጸመባቸው አካውንቶች ማጣራት እስከሚደረግ ድረስ እንዲታገዱ ተደርጓል።
ፕሬዝደንቱ ምን ያህል ወጭ እንደተደረግ ይፋ አላደረጉም።
ባንኩ በሽዎች የሚቆጠሩ የሳይበር ጥቃቶች ማክሸፉን የገለጹት ፕሬዝደንቱ ይህ ችግር የተፈጠረው የሲስተም ማሻሻያ ሲደረግ በተፈጠረ ስህተት ነው ብለዋል።