እስራኤል የጋዛውን ጦርነት በፍጥነት መጨረስ አለባት - ትራምፕ
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እስራኤል በጦርነቱ ምክንያት አለምን እያጣች እንዳትሄድ መጠንቀቅ እንዳለባት ነው ያሳሰቡት
ትራምፕ በዋይትሃውስ ቆይታቸው ለእስራኤል ወሳኝ ውሳኔዎችን ማሳለፋቸው ይታወሳል
የአሜሪካ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል በጋዛ የጀመረችውን ጥቃት በፍጥነት እንድታጠናቅቅ ጠየቁ።
እስራኤል ለጥቅምት 7ቱ የሃማስ ጥቃት የሰጠችውን ምላሽ እኔም በስልጣን ላይ ብሆን የማደርገው ነው ያሉት ትራምፕ፥ ጦርነቱ ጊዜ መውሰዱ ግን የእስራኤልን አለማቀፍ ተቀባይነትና ድጋፍ እያደበዘዘው መሄዱን ተናግረዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ከእስራኤሉ ሃዮም ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ “ጦርነቱ መጠናቀቅ አለበት፣ በዚህ ሁኔታ መቀጠል አይኖርባችሁም፤ እስራኤል አለምን እያጣች እንዳትሄድ መጠንቀቅ አለባት” ነው ያሉት።
ቴል አቪቭ በጋዛ የምትወስዳቸውን እርምጃዎች የሚያሳዩ ምስሎች እና ቪዲዮዎች መልቀቋም የሀገሪቱን ምስል እያበላሸ ነው ማለታቸውን ጋዜጣው አስነብቧል።
ትራምፕ እና ሪፐብሊካን ፓርቲያቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር መልካም የሚባል ወዳጅነት አላቸው።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ወደ ዋይትሃውስ እንደዘለቁ “እየሩሳሌም የእስራኤል መዲና ናት፤ የጎላን ተራሮችም የእስራኤል ይዞታዎች ናቸው” የሚሉ ከአሜሪካ የቀደመ ፖሊሲ ውጭ የሆኑ ውሳኔዎችን ማሳለፋቸው ይታወሳል።
እስራኤል በሃይል በያዘቻቸው የፍልስጤም መሬቶች ላይ የምታካሂደው የሰፈራ ፕሮግራምም ህጋዊ ነው ማለታቸው የኔታንያሁ አስተዳደር ከሪፐብሊካኖች ጋር ያለውን ወዳጅነት አመላካች ነበር።
በህዳር ወር 2024 ዳግም ዋይትሃውስ ለመግባት የሚፎካከሩት ትራምፕም ሆነ በስልጣን ላይ ያሉት ጆ ባይደን፥ እስራኤል በጋዛ የምታካሂደው ጦርነት ተገቢነቱ ላይ አይከራከሩም።
ጦርነቱ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ማስከተሉና በራፋህ ሊጀመር የታሰበው እግረኛ ጦር የማስገባት እንቅስቃሴ ግን በዴሞክራቶችም ሆነ ሪፐብሊካኖች ዘንድ ተቃውሞ እያስነሳ ነው።
አሜሪካ በጸጥታው ምክርቤት ከሶስት ጊዜ በላይ ለእስራኤል ስትከላከል ቆይታ ትናንት ምሽት አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይም ድምጸ ተአቅቦ ማድረጓ የዚህ ማሳያ ነው ተብሏል።
የእስራኤል ባለስልጣናት ግን አሜሪካ ከቀደመ ፖሊሲዋ ውጭ ያሳለፈችው ውሳኔ ቢያበሳጭም ጦርነቱ ይቀጥላል ማለታቸውን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ታሪክ እና በጋዛው ጦርነት ዋሽንግተን ያደረገችውን ድጋፍ የሚጠቅሱ ተንታኞች ግን እስራኤልም ሆነች አሜሪካ የጸጥታው ምክርቤት የተኩስ አቁም ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ ቃላት ቢወራወሩም የሰባት አስርት አመት ግንኙነታቸውን የሚያሻክር አይሆንም ይላሉ።