ባንኩ ችግሩ በተከሰተበት ወቅት ከ490 ሺህ በላይ ዝውውሮች (ግብይቶች) መደረጋቸውን አስታውቋል
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አርብ እለት ያጋጠመውን ችግር አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ በሰጡት መግለጫ፤ ባንኩ ለለደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎትን ለማድረስ ሲል ከ2022 ጀምሮ ለውጦችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀው፤ ያጋጠመው ችግርም ከዚሁ ጋር የተያያዘ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ባሳለፍነው አርብ መጋቢት 6 2016 ዓ.ም ያጋጠመው ችግር የአገልግሎት ማሻሻያ ትግበራ ላይ በተፈጠረ ስህተት መሆኑን እና ችግሩ የውስጥ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ባንኩ በመግለጫው “ችግሩ የተከሰተው አንድ ሂሳብ ማስታረቅ ቅልጥፍና እንዲያመጣ ታስቦ የተሰራ የሲስተም ማሻሻያ ሲተገበር ስህተት በመፈጠሩ እንደሆነ ያስታወቀ ሲሆን፤ የተፈጠረው ስህተትም ለሌቦች ቀዳዳ ከፍቶ ነበር” ብሏል
የሲስተም ማሻሻያው የተተገበረው አርብ መጋቢት 6 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 3 ሰዓት አካባቢ እንደነበረ የገለጸው ባንኩ፤ ከሌሊቱ 8 ሰዓት አካባቢ ችግር እንዳለ መለየቱን ገልጿል።
ይህንን ተከትሎም አንዳንድ የተጠረጠሩ አገልግሎቶች እንዲቋረጡ መደረጉንና ይህም ሆኖ ሙሉ በሙሉ ችግሩ ስላልቆመ ሁሉም የዲጂታል ባንክ ስርዓቶች እንዲቋረጡ ተደርጎ ነበረ ብሏል።
ባንኩ ችግሩ በተከሰተበት ወቅት ከ490 ሺህ በላይ ግብይት መፈፀሙን ያስታወቀ ሲሆን፤ሌሊቱን ሙሉ ግብይት ሲፈጸምባቸው የነበረባቸው የባንክ ሂሳቦች በሙሉ እስኪጣራ ድረስ እንዲታገዱ መደረጉን ገልጿል።
ከፍተኛ እና ያልተገባ ግብይት የፈጸሙ አካላትን እየለየ ለህግ የማቅረብ ስራ መጀመሩንም ነው ባንኩ በመግለጫው ያስታወቀው።
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በወንጀሉ ዋነኛ ተዋናይ መሆናቸው እንዳሳዘነው ያስታወቀው ባንኩ፤ በየአካባቢው ያሉ የዲስትሪክት ሃላፊዎች በየአካባቢው ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት ተማሪዎች የወሰዱትን ገንዘብ እንዲመልሱ እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።
ባንኩ ከተፈጠረው ችግር ጋር ተያይዞ ባጋጠመው አጠቃላይ ጉዳት ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ የችግሩ መሰረታዊ መንስዔ እና ያስከተለውን ጉዳትም ምርመራው ሲጠናቀቅ ይፋ የሚያደርግ መሆኑን አስታውቋል።
ሆኖም ግን “የደረሰው ጉዳት ባንኩ ካለው ሀበት እና አቅም አንጻር የጎላ ተጽእኖ የለውም” ያለ ሲሆን፤ ከደንበኞች ሂሳብ ጋር የማይገናኝ በመሆኑ፤ ደንበኞቹን “ሀሳብ አይግባችሁ” ብሏል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ በመግለጫቸው፤ ባንኩ የሳይበር ጥቃት እንደደረሰበት ተደርጎ በማህበራዊ ሚዲያ የሚዘዋወረው በፍፁም ከእውነት የራቀ እና ባንኩ የሳይበር ደህንነቱ ጠንካራ መሆኑን ገልፀዋል።
ባንኩ ላይ የተለያዩ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች በየጊዜው እንደሚደረጉ እና ባንኩ ባለው እጅግ ጠንካራ የሳይበር ደህንነት ስርዓት እንደሚመከቱ የገልፁት አቶ አቤ አሁን የተፈጠረው ችግር በሲቢኢ ብር እና በሞባይል ባንኪንግ አገልግሎቶች ላይ ተደርጎ በነበረ አዲስ የሲስተም ማሻሻያ ትግበራ ክፍተት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ባንኩ በ2022/23 የበጀት ዓመት ብቻ በአጠቃላይ ከ18 ሺህ በላይ፤ በ2023/24 በጀት ዓመት ደግሞ ከ9 ሺህ 913 በላይ የተቃጡበትን የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችንም ማክሸፉን አስታውቋል።