በ80 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በአዲስ አበባ የተጀመረው የአፍሪካ ሲዲሲ ግንባታ ምን ደረጃ ላይ ደርሷል…?
አፍሪካ በየዓመቱ ከ100 በላይ ወረርሽኞች እና ተላላፊ በሽታዎችን በማስተናገድ ላይ ናት
አፍሪካ በአህጉሪቱ ለሚከሰቱ የጤና እክሎች ክትባቶችን እንድታመርት ማድረግ የማዕከሉ ዋና አላማ ነው
በአዲስ አበባ እየተገነባ ያለው የአፍሪካ በሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል ግንባታ 45 በመቶ መድረሱ ተነግሯል።
ከአንድ ዓመት በፊት በ80 ሚሊየን ዶላር ወጪ ግንባታው የተጀመረው ይህ ማዕከል በአዲስ አበባ ጋርመንት አካባቢ በቻይናው የግንባታ ተቋራጭ በመገንባት ላይ ይገኛል።
ሙሉ ወጪው በቻይና መንግስት ተሸፍኖ እየተገነባ ያለው የአፍሪካ በሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል ወይም ሲዲሲ የግንባታ ደረጃ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን፣ የቻይና መንግስት ተወካዮች፣ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ አምባሳደሮች ተጎብኝቷል።
የአፍሪካ ህብረት የማህበራዊ እና ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር አሚራ ኤል ፋዲ መሀመድ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት የማዕከሉ ግንባታ 45 በመቶ መደረሱን ገልጸዋል።
የአፍሪካ በሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል ግንባታው በፈረንጆቹ ባሳለፍነው ታህሳስ 2020 ዓመት እንደተጀመረ የገለጹት ኮሚሽነር አሚራ የኮሮና ቫይረስ በማዕከሉ ግንባታ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያደርስ ቢገመትም ግንባታው በፍጥነት እየተካሄደ መሆኑን አክለዋል።
ለማዕከሉ ግንባታ እውን መሆን የቻይናን እና የኢትዮጵያ መንግስትን ያመሰገኑት ኮሚሽነር አሚራ ማዕከሉ ሲጠናቀቅ አፍሪካ ከጤና ጋር በተገናኙ ጉዳዮች ያሉባትን ችግሮች በራሷ እንድትፈታ ያስችልታልም ብለዋል።
በአፍሪካ በሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል የፖሊሲ እና ጤና ዲፕሎማሲ ሃላፊ የሆኑት ዶክተር ቤንጃሚን ጁዳልባይ በበኩላቸው ማዕከሉ በሚቀጥለው ታህሳስ 2022 ዓመት ይጠናቀቃል ብለዋል።
የዚህ ማዕከል አላማዎች የወረርሽኝ በሽታዎች የሚያጠኑ ባለሙያዎችን ማፍራት፣ክትባቶችን በራስ አቅም ማምረት፣በክፍለ አህጉራት እና በሁሉም የአፍሪካ አገራት የበሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከላትን ማቋቋም እና ከተለያዩ አህጉራት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የጤና ተቋናት ጋር ትብብርን ማጠናከር እንደሆነም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
የአፍሪካ ሲዲሲ በተለይም በበለጸጉ አገራት ላይ ብቻ የተመሰረተውን የአፍሪካ የክትባት ፍላጎት በራስ አቅም እንዲመረት ማድረግ ትልቁ ስራው መሆኑንም ዶክተር ቤንጃሚን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ማዕከሉ ሲጠናቀቅ አፍሪካ በየዓመቱ እያጋጠማት ያለውን ከ100 በላይ ተላላፊ በሽታዎች እና ወረርሽኞች በራሷ መቆጣጠር እንድትችል ያደርጋታልም ብለዋል ዶክተር ቤንጃሚን።
ከዚህ በተጨማሪም በተለይም አሁን በአፍሪካ ያሉትን ሁለት ሺህ የወረርሽኝ በሽታዎች ተመራማሪዎች ቁጥር ወደ 6 ሺህ እና ከዛ በላይ ማድረስም ያስችላል ብለዋል።