አሜሪካ ጦርነቱ ጋብ ብሎ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ ጥሪ እያቀረበች ሲሆን ሩሲያ ግን የሰብአዊ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ትፈልጋለች
አሜሪካ እና ሩሲያ በእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት ችግር ውስጥ ያሉ ፍልስጤማውያን እርዳታ ለማግኘት ያስችሏቸዋል ያሏቸውን የሚቃረኑ ሀሳቦች ለተመድ አቅርበዋል።
ሁለቱ ሀገራት ተኩሱ ይቁም ወይስ ጋብ ይበል በሚለው ጉዳይ እየተከራከሩ ይገኛሉ።
ነገርግን ሁለቱም ሀገራት የተመድ የውሳኔ ሀሳብ በጋዛ ያለውን የመብራት፣ የውሃ እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ችግር እንዲፈታ እንደሚፈልጉ ሮይተርስ ዘግቧል።
አሜሪካ ጦርነቱ ጋብ ብሎ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ ጥሪ እያቀረበች ሲሆን ሩሲያ ግን የሰብአዊ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ትፈልጋለች።
ጦርነቱን ጋብ ማድረግ መደበኛ ያልሆነ እና ከተኩስ አቁም ያነስ ጊዜ ነው። ዋነኛ የእስራኤል አጋር የሆነችው አሜሪካ ጦርነቱ ጋብ እንዲል እንደምትፈልግ 15 አባላት ላሉት የጸጥታው ምክርቤት ባቀረበችው ረቂቅ ሰነድ ላይ ጠቅሳለች።
ሩሲያ፣ የአሜሪካን የመፍትሄ ሃሳብ እንደማትደግፍ እና ተኩስ አቁም እንዲደረግ የሚጠይቅ የራሷን ሀሳብ እንደምታቀርብ ባለፈው ማክሰኞ እለት መግለጿ ይታወሳል።
ሩሲያ ያቀረበችው የተኩስ አቁም መፍትሄ በአረብ ሀገራት የሚደገፍ ነው።
የጸጥታው ምክርቤት የውሳኔ ሀሳብ በትንሹ የዘጠኝ ሀገራት ድጋፍ እና ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት(ቬቶ) ካለቸው ሀገራት ምንም ተቃውሞ ካላጋጠመው ይጸድቃል።
ባለፈው ሳምንት አሜሪካ የሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ ጦርነቱ ጋብ እንዲል በብራዚል የቀረበውን ሀሳብ ቬቶ በማድረጓ ሳይጸድቅ ቀርቷል።
አሜሪካ ባለፈው ቅዳሜ እስራኤል ራሷን የመከላከል መብት አላት የሚል ይዘት ያለው ረቂቅ ሰነድ አቅርባ የተወሰኑ ሀገራትን ዲፕሎማቶችን አስደንግጣለች።
መጀመሪያ ላይ አሜሪካ ጦርነቱ ጋብ እንዲልም ቢሆን ጥሪ አላቀረበችም ነበር።
ነገርግን አለምአቀፍ ጫና ሲበረታባት ሰነዷን በማሻሻል ለሰብአዊ እርዳታ ጦርነቱ ጋብ እንዲል የሚጠይቅ ሀሳብ አካታለች።
የሀማስን ያልተጠበቀ እና ከባድ የተባለውን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል እያደረሰች ያለውን የአጸፋ እርምጃ አጠናክራ ቀጥላለች።
እስራኤል ያለማቋረጥ በአየር እየደበደበች ሲሆን ጋዛን ከባ በእግረኛ ወታደር ጥቃት ለመክፈት ተዘጋጅታለች።
የአረብ ሀገራት ተኩስ እንዲቆም ጥሪ እያቀረቡ ሲሆን አሜረካን ጨምሮ ምዕራባውያን ሀገራት ስለተኩስ አቁም ማውራት አልፈለጉም።