እስራኤል በሀማስ ለታገቱባት ዜጎቿ መረጃ ለሚሰጧት ጉርሻ አቀረበች
ቴላቪቭ መረጃ ለሚሰጧት ጉርሻና ጥበቃ እንደምትሰጥ በጋዛ በበተነችው በራሪ ወረቀት ገልጻለች
የእስራኤል ባለስልጣናት ታጋቾች በጋዛ ዋሻዎች ውስጥ ተይዘው ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል
የእስራኤል ጦር በጋዛ በራሪ ወረቀቶችን በመበተን በሀማስ ስለታገቱ ዜጎች መረጃ ለሚሰጡ ጥበቃ እና ሽልማት እሰጣለሁ ብሏል።
የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ከሁለት ሳምንታት በፊት ባደረሰው ጥቃት አንድ ሽህ 400 ሰዎችን ሲገድል፤ ከ200 በላይ ሰዎችን ደግሞ አግቶ ወስዷል።
"በሰላም ለመኖር እና ለልጆቻችሁ የተሻለ የወደፊት ህይወት የምትፈልጉ ከሆነ ወዲያውኑ ሰብዓዊ ተግባር ፈጽሙ። እናም በአካባቢያችሁ ስለሚገኙ ታጋቾች የተረጋገጡ እና ጠቃሚ መረጃዎችን አካፍሉ" ሲል ጦሩ በበራሪ ወረቀቱ ላይ ተናግሯል።
"የእስራኤል ጦር የእርስዎን እና የቤትዎን ደህንነት ለመጠበቅ ከፍተኛውን ጥረት እንደሚያደርግ እና የገንዘብ ሽልማት እንደሚሰጥ ያረጋግጥልዎታል። ሙሉ ምስጢራዊነትዎንም እናረጋግጣለን" በማለት አክሏል።
ሮይተርስ እንደዘገበው በራሪ ወረቀቱ ለመረጃ ሰጭዎች እንዲደውሉ የስልክ ቁጥሮችን ዘርዝሯል።
የውጭ ዜጎችን ጨምሮ ታጋቾቹ ወደ ጋዛ መወሰዳቸውን እስራኤል የገለጸች ሲሆን፤ ነገር ግን ታጋቾቹ የት እንዳሉ በትክክል አለመታወቁ ነጻ የማውጣት ስራውን ውስብስብ አድርጎታል።
ባለስልጣናቱ ታጋቾቹ በጋዛ ስር ባሉ ዋሻዎች ውስጥ ተይዘው ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
ሀማስ ከሰሞኑን አራት ታጋቾችን የለቀቀ ሲሆን፤ ተጨማሪ ታጋቾችን አስቻይ ሁኔታ ሲኖር ለመልቀቅ ቃል ገብቷል።