ሱዳን ተመድ የፖለቲካ ተልእኮውን በአስቸኳይ እንዲያቋርጥ ጠየቀች
ዩኤንአይቲኤም በሱዳን ስራውን የጀመረው በፈረንጆቹ 2020 ሲሆን 400 ሰራተኞችን ቀጥሮ እየሰራ ይገኛል
ደብዳቤው ተልእኮው የተቋቋመው በሰዳን የተከሰተውን አብዮት ተከትሎ ያለውን ሽግግር ለማገዝ ቢሆንም ውጤቱ "ቅር የሚያሰኝ" መሆኑን ጠቅሷል
ሱዳን ተመድ የፖለቲካ ተልእኮውን በአስቸኳይ እንዲያቋርጥ ጠየቀች።
የሱዳን መንግስት በጻፈው ደብዳቤ ተመድ በሀገሪቱ ያለውን የፖለቲካ ተልእኮ በአስቸኳይ እንዲያቋርጥ መጠየቁን ሮይተርስ ዘግቧል።
"የሱዳን መንግስት ተመድ በአስቸኳይ የተመድ ኢንተግሬትድ ትራንዚሽን አሲስታንስ ሚሽንን (ዩኤንአይቲኤሚ) እንዲያቋርጥ ጠይቋል። በዚህ ወቅት የሱዳን መንግስት ከጸጥታው ምክርቤት ጋር ገንቢ በሆነ መልኩ ለመወያየት እንደሚችል እናረጋግጣለን" ሲሉ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሊ ሳድቅ ለጸጥታው ም/ቤት ተናግረዋል።
ዩኤንአይቲኤም በሱዳን ስራውን የጀመረው በፈረንጆቹ 2020 ሲሆን 400 ሰራተኞችን ቀጥሮ እየሰራ ይገኛል።
ለተመድ ዋና ጸኃፊ የተላከው ይህ ደብዳቤ ተልእኮው የተቋቋመው በሰዳን በፈረንጆቹ 2018 የተከሰተውን አብዮት ተከትሎ ያለውን ሽግግር ለማገዝ ቢሆንም ውጤቱ "ቅር የሚያሰኝ" መሆኑን ጠቅሷል።
የተመድ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ቃል አቀባይ ደብዳቤው እንደደረሳቸው እና ለጸጥታው ም/ቤት መተላለፉንም አረጋግጠዋል።
በሱዳን በጀነራል አል ቡርሃን እና በጀነራል ሀምዳን ደጋሎ ወይም ሄሜቲ መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ሱዳን ከአልበሽር መወገድ በኋላ የገባችበት ቀውስ ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲደርስ አድርጎታል።
ጦርነቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶችም ምንም ውጤት አላመጡም።