ሶማሊያና ኬንያ ወደ ንግግር እንዲመጡ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር አሳሰቡ
ሙሳ ፋኪ፡ “ኢጋድ የተባበረች አፍሪካ እውን እንድትሆን የሚበቅበትን ሚና ይወጣል የሚል እምነት አለኝ”
ሶማሊያውያን ዕጣ ፋንታቸውንና ሀገራቸውን በእጃቸው ማስገባት እንዳለባቸው ሊቀመንበሩ ተናግረዋል
በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ የሚገኘውን የአፍሪካ ቀንድ ወደ መረጋጋት ለማምጣት ኢጋድ ከፍተኛ ጥረት ሊያደርግ እንደሚገባም የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት አሳስበዋል፡፡
ከሰሞኑ አለመግባባት ውስጥ የገቡት ሞቃዲሾ እና ናይሮቢ ከገቡበት እሰጥ አገባ እንዲወጡና ንግግር እንዲጀምሩ የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጠይቀዋል፡፡
በጅቡቲው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ልዩ ስብሰባ ላይ የታደሙት ሊቀመንበሩ የሁለቱ ሀገራት ሕዝብ ግንኑነት አሁን የተከሰተውን ችግር የመፍታት አቅም እንዳለው አስታውቀዋል፡፡ ኬንያ የአፍሪካ ሕብረት የሶማሊያ ተልዕኮ (አሚሶም) ውስጥ በመሳተፍ ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን የምታዋጣ ሀገር በመሆኗ እና በርካታ የሶማሊያ ስደተኞችን በመያዟ ግንኙነታቸው ከፍተኛ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ ሁለቱም ወገኖች በንግግር አለመግባባታቸውን እንዲፈቱ ኢጋድ ድጋፍ ማድረግ አለበትም ብለዋል ሊቀመንበሩ፡፡ ለጉዳዩ የአፍሪካ ሕብረትም ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጠው በማንሳት ፣ ችግሩ ግን በቀጣናዊው ድርጅት ኢጋድ በኩል መፍትሄ እንደሚያገኝ ገልጸዋል፡፡
አፍሪካ ከዚህ በኋላ ለክፍፍልና ለጸብ መነሳት የለባትም ያሉት ሙሳ ፋኪ ማሃማት ኢጋድ የወደፊቷ አፍሪካ ሰላም የሰፈነባት፣ የተባበረችና የበለጸገች እንድትሆን የሚጠበቅበትን ሚና እንደሚወጣም ገልጸዋል፡፡ ከኬንያ ጋር ግንኙነቴን አቋርጫለሁ ያለችው ሶማሊያ ዲፕሎማቶቿ እንዲወጡ ማዘዟን ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት መካከል መካረሩ አይሎ ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም ሁለቱን ሀገራት የሸማገሉት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከኢጋድ ጉባዔ ጎን ለጎን ከሶማሊያ እና ከኬንያ መሪዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ በሱዳን ያለውን ሁኔታ በተመለከተም ሀሳብ የሰጡ ሲሆን በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ሽግግሩ እየተካሄደ እንደሆነ ጠቅሰው በርካታ ችግሮች በመኖራቸው ትብብርና ወንድማማችነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በዚህ ወቅት አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ ሱዳን ሽብርን ከሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ መውጣቷ ትልቅ እርምጃ መሆኑን የገለጹት ሙሳ ፋኪ ይህም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከቀሪው ዓለም ጋር እንዲተሳሰር ያደርጋል ብለዋል፡፡
ደቡብ ሱዳንን በተመለከተ በሀገሪቱ ሰላምና ጸጥታን ለማረጋገጥ አሁንም የተጀመረው ጥረት እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡ በሶማሊያም ሽብርተኝነትን የመከላከል ስራ እና የፌዴራል ተቋማትን ማጠናከር መሻሻል ቢያሳይም አሁንም ግን ፈተና እየገጠመው ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አሚሶም በሶማሊያ ከ 10 ዓመት በላይ መቆየቱን አንስተው ሶማሊያውያን አሁን ዕጣ ፋንታቸውንና ሀገራቸውን በእጃቸው ማስገባት አለባቸው ብለዋል፡፡ ይህ ማለት በአሚሶም ስር የነበረውን ጸጥታ የማስጠበቅ ስራ ወደ ሶማሊያ ብሔራዊ ጦር እንዲገባ የማድረግን ዕቅድ የሚደግፍ ነው፡፡ ሶማሊያውያን በሰላምና በደህንነት የመኖር መብትና ፍላጎት አላቸው ያሉት ኮሚሽነሩ ለዚህም በቅርቡ በሀገሪቱ የሚደረገው ምርጫ ተአማኒ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎች መመቻቸት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የወሰደው እርምጃ ሕጋዊ መሆኑንም ሙሳ ፋኪ ገልጸዋል፡፡