ሶማሊያ ከኬንያ ጋር ያላትን ግንኙነት ማቋረጧን ገለጸች
ሀገሪቱ እርምጃውን የወሰደችው የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ወደ ናይሮቢ ማቅናታቸውን ተከትሎ ነው
ሶማሊያ በአንድ ሳምንት ውስጥ ዲፕሎማቶቿ ከኬንያ እንዲወጡ አዛለች
ሶማሊያ ከጎረቤቷ ኬንያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋረጧን የሀገሪቱ መንግስት አስታውቋል፡፡
ሞቃዲሾ በሉዓላዊነቴ ላይ ‘ግልፅ ጣልቃ ገብነት’ እየፈጸመች ነው በሚል ነው ከናይሮቢ ጋር ግንኙነቷን ማቋረጧን የገለጸችው፡፡
የሶማሊያ ፌዴራል መንግስት ሰኞ ማምሻውን በሰጠው መግለጫ ከኬንያ ጋር ያለው ግንኙነት መቋረጡን እና በኬንያ ያሉ የሶማሌ ዲፕሎማቶች በሙሉ በሰባት ቀናት ውስጥ ሀገሪቱን ለቀው እንደሚወጡ ይፋ አድርጓል፡፡
የሶማሊያ ማስታወቂያ ሚኒስትር ኦስማን ዱቤ በብሔራዊ ቴሌቪዢን ጣቢያ ቀርበው "የሶማሊያ ፌዴራል መንግስት ይህንን ውሳኔ የወሰደው የኬንያ መንግስት በሀገራችን ሉዓላዊነት ላይ በተደጋጋሚ ለሚፈፅማቸው የፖለቲካ ጥሰቶች እና ግልፅ ጣልቃ ገብነት ምላሽ ለመስጠት ነው" ብለዋል፡፡
ሶማሌ ይህን እርምጃ የወሰደችው የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ናይሮቢ አቅንተው ከኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር መነጋገራቸውን ተከትሎ ነው፡፡ ሁለቱ መሪዎች ‘በጋራ ጉዳዮች’ ላይ መነጋገራቸውን እና ውይይታቸውም እንደሚቀጥል የኬንያ መንግስት አስታውቋል።
ኬንያ እና ሶማሊያ ላለፉት አራት ዓመታት ዲፕሎማሲያዊ ግጭት ውስጥ የቆዩ ሲሆን እ.ኤ.አ. ባለፈው ህዳር ወር መጨረሻ በሶማሊያ የኬንያ አምባሳደር መባረራቸውን ተከትሎ የሀገራቱ ውጥረት አይሏል፡፡
ዛሬ በጋራ መግለጫ ይጠናቀቃሉ ተብሎ የሚጠበቀውን የኬንያታና ቢሂ የውይይት ውጤት ሞቃዲሾ በትኩረት እየተከታተለች እንደምትገኝ የሀገሪቱ ሚዲያ ጉብጁግ ዘግቧል፡፡