የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል የወሰደው እርምጃ ሕጋዊ መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ገለጹ
የኢጋድ አባል ሀገራት መሪዎችም የፌዴራል መንግስት ለወሰደው እርምጃ ዕውቅና መስጠታቸውን ጠ/ሚ ዐቢይ ገልጸዋል
የፌዴራል መንግሥት ሕገ-መንግስታዊ ስርዓትን ለማስጠበቅ ቆራጥ እርምጃ መውሰዱን ሊቀመንበሩ ተናግረዋል
በትናንትናው ዕለት በጅቡቲ በተካሔደው የኢጋድ የመሪዎች ልዩ ስብሰባ ላይ የተሳተፉት የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ንግግር አድርገዋል፡፡
የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ባደረጉት ንግግር የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል የወሰደው እርምጃ ተቀባይነት ያለው ሕጋዊ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
“በኢትዮጵያ የፌዴራሉ መንግሥት የሀገሪቱን አንድነት እና መረጋጋት እንዲሁም ሕገ-መንግስታዊ ስርዓትን ለማስጠበቅ ቆራጥ እርምጃዎችን ወስዷል” ያሉት ሊቀመንበሩ ይህም ለሁሉም ሀገራት የሚሰራ ሕጋዊ እርምጃ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ይሁንና “በትግራይ የተፈጠረው ቀውስ ከፍተኛ መፈናቀልን ማስከተሉ ሊካድ አይችልም” ብለዋል፡፡ በመሆኑም ኢጋድ ሰብአዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ኢትዮጵያን እንዲደግፍ የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ጠይቀዋል፡፡ ለስደተኞች እና ለተፈናቀሉ ዜጎች ልዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም ነው ሊቀመንበሩ ሙሳ ፋኪ ያሳሰቡት፡፡
ኢትዮጵያ በክቀጣናው በሰላም ማስከበር ሥራዎች የምትጫወተውን ወሳኝ ሚና ማስታወስ አስፈላጊ ነው ያሉት ሙሳ ፋኪ እነዚህ ጥረቶች እንደሚቀጥሉ ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉምለኢትዮጵያ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የአፍሪካ ቀንድ በጣም የተለየ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ እና ይህም ኢጋድን የተለያዩ ከባድ ፈተናዎችን እንዲጋፈጥ እንዳስገደደውም ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደግሞ ፣ የኢጋድ አባል ሀገራት መሪዎች በትግራይ ክልል ለተከናወነው የህግ ማስከበር ሥራ እውቅና መስጠታቸውን ትናንት ታህሣሥ 11 ቀን 2013 ዓ.ም ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይ አሕመድ በፌስቡክ ገጻቸው "የኢጋድ አባል ሀገራት መሪዎች የህግ ማስከበር እርምጃዎቻችንን ህጋዊነት በመረዳታቸውና እውቅና በመስጠታቸው እንዲሁም ኢትዮጵያን ለመደገፍ ቁርጠኝነታቸውን በመግለፃቸው እጅግ ጥልቅ ምስጋናዬን አቀርባለሁ" ብለዋል፡፡
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ በሕወሓት ኃይል ጥቃት መፈጸሙ ይፋ መደረጉን ተከትሎ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ በሦስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ መቐሌን መቆጣጠሩ ይታወቃል፡፡
የሕግ ማስከበር እና የህልውና ዘመቻው መጠናቀቁን የገለጸው የፌዴራል መንግሥት በቀጣይነት በወንጀል የሚፈለጉ የሕወሓት አመራሮችን እና ከመከላከያ ሠራዊት የከዱ አመራሮችን የማደን ተግባር በማከናወን ላይ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
በወንጀል የሚፈለጉ የሕወሓት አመራሮች የሚገኙበትን ስፍራ ለተቆመ ግለሰብ የመከላከያ ሠራዊት የ10 ሚሊዮን ብር ሽልማት እንደሚሰጥም ገልጿል፡፡