ሶማሊያ ናይሮቢ የሚገኙ ሁሉም ዲፕሎማቶቿ እና ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ አዘዘች
ኬንያ በበኩሏ ስለጉዳዩ ይፋዊ መግለጫ እንዳልደረሳት እና ግንኙነታቸውን ለማደስ እንደምትሰራ አስታውቃለች
ከኬንያ ጋር ግንኙነቴን አቋርጫለሁ ያለችው ሶማሊያ ዲፕሎማቶቿ ከናይሮቢ በ5 ቀናት ውስጥ እንዲወጡ አዛለች
የፕሬዚዳንት ሞሃመድ ፋርማጆ መንግሥት በኬንያ የሚገኙ ሁሉም የሶማሊያ ዲፕሎማቶች እና ቤተሰቦቻቸው በአምስት ቀናት ውስጥ ሀገሪቱን ጥለው ወደ ሶማሊያ እንዲመለሱ አዟል፡፡
ሶማሊያ ምርጫ ለማድረግ በተሰናዳችበት በዚህ ጊዜ የስልጣን ጊዜው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የፕሬዝዳንት ፋርማጆ መንግስት ፣ የሶማሊያን ሉዓላዊነት በመጣስ “በውስጥ ጉዳዬ ጣልቃ እየገባችብኝ ነው” በማለት ኬንያን በመክሰስ ላይ ይገኛል፡፡
በተለይ ደግሞ ሶማሊያ እንደ አንድ ግዛቷ የምትቆጥረው የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ከትናንት በስቲያ በኬንያ ጉብኝት አድርገው ከፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር በሁለትዮሽ የትብብር ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ተከትሎ ፣ ሶማሊያ ከኬንያ ጋር ያላትን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ማቋረጧን አስታውቃለቸ፡፡
የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኬንያ ጋር ያለውን ግንኙነት ካቋረጠ እና ኤምባሲውን ከዘጋ ከቀናት በኋላ ቀሪዎቹ ሰራተኞች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በትናንትናው ዕለት ነው መመሪያ የሰጠው፡፡ ይህም የሀገራቱ ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ መሻከሩን የሚያመለክት እንደሆነ የሶማሊያው ጉብጁግ ዘገባ ይገልጻል፡፡
የሀገራቱን ግንኙነቶች መቋረጥ እና ሌሎች እርምጃዎችን በተመለከተ ይፋዊ መግለጫ ከሞቃዲሾ ለናይሮቢ አልደረሰም ያለው የኬንያ መንግስት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጠው ለሶማሊያ መንግሥት በደብዳቤ እንደፃፈም በዘገባው ተካቷል፡፡
ለሶማሊያ ውሳኔ ተመሳሳይ ምላሽ መስጠትን ያልመረጠችው ኬንያ የሻከረውን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ መደበኛው ለመመለስ የሚረዳ ቡድን እንደምታቋቁም አስታውቃለች፡፡