ትራምፕ ለአፍሪካ ሀገራት የሚደረገው ድጋፍ በጊዜያዊነት እንዲቆም ያሳለፉት ውሳኔ እና ተጽዕኖው ምን ይመስላል?
ፕሬዝዳንቱ ወሳኝ የአሜሪካ አጋሮች እስኪመረጡ ድረስ ለአፍሪካ ሀገራት የሚሰጠው ድጋፍ እንዲቆም በስልጣናቸው የመጀመሪያ ቀን ወስነዋል
በ2024 ብቻ አሜሪካ ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ ሀገራ 6.6 ቢሊዮን ዶላር የሰብአዊ እርዳታ ሰጥታለች
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለአፍሪካ የሚደረግ ድጋፍ እንዲቋረጥ የፈረሙት የአስፈፃሚ ትዕዛዝ በአሜሪካ የሰብአዊ እርዳታ ላይ በእጅጉ በሚተማመኑ የአፍሪካ ሀገራት ላይ ሊኖረው የሚችለው ተጽዕኖ ስጋትን ጭሯል፡፡
የትራምፕ ድጋፍን የማቋረጥ ውሳኔ አሁን ያሉ ግጭቶችን ሊያጠናክር ፣ ተጨማሪ ሰብአዊ ተግዳሮቶችን ሊፈጥር እና ችግር ባላባቸው አካባቢዎች አለመረጋጋትን ሊያባብስ እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡
ፕሬዝዳንቱ ሀገራት ከፖሊሲ ግቦቻቸው ጋር ያላቸውን ትስስር ለመገምገም ሁሉንም የአሜሪካ የውጭ እርዳታ ፕሮግራሞች ለ90 ቀናት እንዲታገዱ በስልጣናቸው የመጀመሪያ ቀን ወስነዋል፡፡
በዚህ የ3 ወራት የግምገማ ጊዜ ውስጥ የአሜሪካ የውጭ ዕርዳታ መርሃ ግብሮች ከትራምፕ ፖሊሲ ዓላማዎች ጋር የሚጣጣሙ መሆን አለመሆናቸውን በማጣራት በተወሰኑ ሀገሮች ወይም ፕሮግራሞች የድጋፍ መቀጠል እና ማቋረጥን የሚያስከትል ነው፡፡
ትራምፕ የፈረሙት ሰነድ "በርካታ የውጭ ዕርዳታዎች ከአሜሪካውያን ፍላጎት ጋር የማይጣጣሙ እና ከሀገሪቱ እሴቶች ጋር የሚቃረኑ ናቸው ፤ በሀገሮች ውስጥ እና በሀገሮች መካከል እርስ በርስ የሚስማሙ እና የተረጋጋ ግንኙነቶችን የሚቃረኑ ሀሳቦችን በማስተዋወቅ የዓለምን ሰላም ለማደፍረስ እያገለገሉ ነው " ይላል፡፡
በተጠናቀቀው 2024 ብቻ አሜሪካ ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ ሀገራት 6.6 ቢሊዮን ዶላር የሰብአዊ እርዳታ ሰጥታለች፡፡
ረሃብንና መፈናቀልን ጨምሮ ከባድ ሰብዓዊ ቀውሶችን እያስተናገዱ ያሉ ደቡብ ሱዳን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሶማሊያ የመሳሰሉ ሀገራት በዚህ ውሳኔ ከአሜሪካ የሚደረግላቸውን ወሳኝ ድጋፍ ሊያጡ ይችላሉ።
የገንዘብ ድጋፉ መቋረጥ ሀገራት አስፈላጊ አገልግሎቶችን ለመጠበቅ፣ሰብአዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት እና የልማት ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ተግዳሮት ይሆንባቸዋል ነው የተባለው፡፡
ኮንግረሱ ጥልቅ ቅነሳውን ካፀደቀ፣ የአፍሪካ ድርቅ እና የረሃብ ቀውሶች ሊባባሱ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ፣ ይህም ወደ አውሮፓ የሚደረገውን ፍልሰት እንዲያድግ እና የአክራሪ ቡድኖች ድጋፍ እንዲጨምር ያደርጋል በሚል አስግቷል፡፡
የአለም ምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) መረጃ እንደሚያመላክተው በ2022 በአፍሪካ 282 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች (20 በመቶ የአህጉሪቷ ህዝብ) የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ገጥሞታል፤ ይህም ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወዲህ በ57 ሚሊዮን ከፍ ያለ ነው፡፡
በአህጉሪቱ ወደ 868 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ የምግብ ዋስትና ችግር አጋጥሟቸዋል ፤ ከአንድ ሶስተኛ በላይ ወይም 342 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ባለፈው አመት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በአንጎላ ጉብኝታቸው ወቅት በ31 የአፍሪካ ሀገራት የምግብ ዋስትናን እና ሰብአዊ እርዳታዎችን ለመደገፍ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ሰብአዊ ርዳታ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።
በግጭት፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በኢኮኖሚ አለመረጋጋት የተነሳ በናይጄሪያ፣ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ያሉ የሰብአዊ ቀውሶች አሁንም አሳሳቢ ናቸው።
በናይጄሪያ 25 ሚሊዮን ሰዎች በሰሜን ምስራቅ ግጭት እና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት የምግብ ዕጥረት፣ መፈናቀል እና ውስን የጤና አጠባበቅ አጋጥሟቸዋል ፈተና ሆኖባታል፡፡
በሶማሊያ በግጭቶች እና እንደ ድርቅ እና ጎርፍ ያሉ የአየር ንብረት አደጋዎች ምክንያት 8.3 ሚሊዮን ሰዎች ለችግር ተዳርገዋል፤ በዚህም አጣዳፊ የምግብ እጥረት እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተስፋፍቷል።
ጤና በተመለከተ በአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤአይዲ) እና በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በሚደገፉ በርካታ ፕሮግራሞች በአፍሪካ የጤናውን ዘርፍ የረጅም ጊዜ አጋር ሆነው ዘልቀዋል፡፡
ዋሽንግተን ለአፍሪካ አህጉር በዓመት ወደ 8 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ የምታደርግ ሲሆን ፤ ከዚህ ውስጥ 70 በመቶው ወይም 5.6 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ለጤና ሴክተር ፕሮግራሞች የሚሰጥ ነው።
በአሜሪካ የአፍሪካ የደህንነት ትብብር ዘርፍ ጸጥታን፣ ጸረሽብርተኝነትን እና ቀጣናዊ መረጋጋትን ለማሻሻል የአፍሪካ ወታደራዊ ሃይሎችን ትደግፋለች።
የአሜሪካ የውጭ ወታደራዊ ፋይናንሲንግ (ኤፍ ኤም ኤፍ) በተባለው ማዕቀፍ በአፍሪካ ውስጥ ሽብርተኝነት ለመዋጋት ፣ የሰላም ማስከበርን እና የድንበር እና የባህር ላይ ደህንነትን ለመደገፍ በርካታ ገንዘብ መድባለች።
ለምሳሌ እ.ኤ.አ ከ2019 እስከ 2023 በአሜሪካን አለም አቀፍ ወታደራዊ ትምህርት እና ስልጠና ፕሮግራም ናይጄሪያ 5 ሚሊዮን ዶላር አግኝታለች። ይህም ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ ድርሻ ያለው ነው።