የየመኑ ታጣቂ ቡድን ለፍልስጤማውያን አጋርነቱን ለማሳየት በሚል በቀይ ባህር በሚያልፉ መርከቦች ላይ ከ100 በላይ ጥቃቶችን አድርሷል
የየመኑ ሃውቲ ከአንድ አመት በላይ በፊት በቁጥጥር ስር ያዋሏት መርከብ ሰራተኞችን መልቀቃቸው ተሰማ።
"ጋላክሲ ሊደር" እቃ የተሰኘችው እቃ ጫኝ መርከብ ሰራተኞች የተለቀቁት የእስራኤልና ሃማስ ተኩስ አቁም ስምምነት አራተኛ ቀኑን በያዘበት ወቅት ነው።
የሃውቲዎች የቴሌቪዥን ጣቢያ አል ሚስራህ 25ቱ የመርከቧ ሰራተኞች ለኦማን ተላልፈው መሰጠታቸውን ዘግቧል።
"ጋላክሲ ሊደር" በየመን የባህር ዳርቻ በሃውቲዎች ቁጥጥር ስር የዋለችው የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ ከአንድ ወር በኋላ በህዳር 2023 ነበር።
የየመኑ ቡድን መርከቧን እና ሁሉንም ሰራተኞቿን ከሄሊኮፕተሮች በመውረድ የያዘው ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላት በማለት ነው።
የመርከቧ ባለቤት ሬይ ካር ኬሪየርስ የተሰኘው የብሪታንያ ኩባንያ በእስራኤላዊው ባለሃብት አብርሃም "ራሚ" ኡንጋር የተቋቋመ ነው።
የባሃማስ ሰንደቅ አላማ የምታውለበልበው "ጋላክሲ ሊደር" ከቱርክ ወደ ህንድ በመጓዝ ላይ እያለች በሃውቲዎች በቁጥጥር ስር መዋሏም ይታወሳል።
እስራኤል ግን መርከቧ የብሪታንያ ኩባንያ ንብረት መሆኗንና በጃፓን ኩባንያ እንደምትተዳደር እንዲሁም አንድም እስራኤላዊ በመርከቧ ውስጥ እንዳልነበር በመጥቀስ በሃውቲዎች መያዟን መቃወሟ አይዘነጋም።
ከኢራን ድጋፍ እንደሚደረግለት የሚነገርለት የየመኑ ቡድን እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን "ጭፍጨፋ" ለማስቆምና ለፍልስጤማውያን አጋርነቱን ለማሳየት በሚል ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው ባላቸው መርከቦች ላይ የሚሳኤልና ድሮን ጥቃቶችን ሲፈጽም ቆይቷል።
ከህዳር 2023 ጀምሮ በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ በሚያልፉ የንግድ መርከቦች ላይ ከ100 በላይ ጥቃቶችን አድርሷል።
በቡድኑ ጥቃት የተፈጸመባችው ሁለት መርከቦች መስጠማቸውም የሚታወስ ነው።