ፈረንሳይ በበሽር አል አሳድ ላይ አዲስ የእስር ማዘዣ አወጣች
አሳድ በፈረንጆቹ 2017 በደራ ከተማ ንጹሃን ያለቁበት ጥቃት እንዲፈጸም በማዘዝ በጦር ወንጀል ተሳትፈዋል በሚል ነው የእስር ማዘዣው የወጣባቸው
የአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት ዋና አቃቤህግ ካሪም ካን በቅርቡ ከሶሪያ አዲሱ አስተዳደር ጋር መክረዋል
ፈረንሳይ በቀድሞው የሶሪያ ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ላይ ሁለተኛውን የእስር ማዘዣ አወጣች።
የፈረንሳይ የወንጀል መርማሪ ቡድን አሳድ የሶሪያ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ በነበሩበት ወቅት በደራ ከተማ በ2017 ንጹሃን ያለቁበትን የቦምብ ጥቃት እንዲፈጸም አዘዋል በሚል ነው የእስር ትዕዛዙን ያወጣው።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት በጦር ወንጀል የሚያስጠይቅ ተግባር በመፈጸም ተጠርጥረው የእስር ማዘዣው መውጣቱንም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ግለሰብን ዋቢ አድርጎ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
የፈረንሳይ እና ሶሪያ ዜግነት ያለው ሳላህ አቡ ናቡር በሰኔ 7 2017 በደራ መገደሉን ተከትሎ ምርመራ ሲካሄድ ቆይቷል።
የሶሪያ ጦር በነሃሴ ወር 2013 በዱማ እና ምስራቃዊ ጉታ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎችን የገደለ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ጥቃት አድርሷል በሚል የፈረንሳይ መርማሪዎች ምርመራ መጀመራቸውም ይታወሳል።
የአሳድ መንግስት ከመጋቢት 2011 ጀምሮ በተቀሰቀሰው ተቃውሞና በ13 አመቱ የእርስ በርስ ጦርነት የኬሚካል ጦር መሳሪያዎችን አለመጠቀሙን ቢገልጽም በተለያየ ጊዜ በወጡ የምርመራ ዘገባዎች መጋለጡን ሬውተርስ አውስቷል።
የፈረንሳይ ዳኞችም በህዳር ወር 2023 አሳድን በሰብአዊነት ላይ በተፈጸመ ወንጀልና የጦር ወንጀል እንዲፈጸም በመፍቀድ ጠርጥረው የእስር ማዘዣ እንዲወጣ አድርገው ነበር።
ይሁን እንጂ አሳድ በወቅቱ ስልጣን ላይ ስለነበሩና በሀገር መሪነታቸው ያለመከሰስ መብታቸው ሊጠበቅ ይገባል የሚል ክርክር በመነሳቱ ተፈጻሚነቱ በእንጥልጥል ቀርቷል።
አሳድ በታህሳስ ወር 2024 በሃያት ታህሪር አል ሻም ታጣቂ ቡድን የተመሩ አማጺያን ከስልጣናቸው ተነስተው ወደ ሞስኮ መኮብለላቸውን ተከትሎ ግን ያለመከሰስ መብታቸው አብቅቶለታል።
በመሆኑም አሳድን ጨምሮ ስድስት በእርሳቸው ዘመን ያገለገሉ ባለስልጣናት ከ2018 ጀምሮ ሲካሄድ በቆየው ምርመራ ምክንያት የእስር ማዘዣ ወጥቶባቸዋል ነው የተባለው።
የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ መረጃ እንደሚያመላክተው ፓሪስ እስካሁን በሶሪያ አመራሮች ላይ ያወጣችው የእስር ማዘዣ 14 ደርሷል።
ስድስት አመት በፈጀው ምርመራ በጦር ወንጀል ሳይሳተፉ አይቀርም ተብለው የተጠረጠሩ የቀድሞ የሶሪያ መሪዎች ክስ ተመስርቶባቸው ተገቢውን ቅጣት ያገኙ ዘንድ የኬሚካል ጥቃቱ ተጎጂ ቤተሰቦች ይጠይቃሉ።
የአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት ዋና አቃቤህግ ካሪም ካን ባለፈው ሳምንት አርብ ከሶሪያ አዲሱ መሪ አህመድ አል ሻራ ጋር መምከራቸው የሚታወስ ነው።
የካሪም ጉብኝት በአሳድ አገዛዝ ወቅት ለተፈጸሙ ወንጀሎች ተጠያቂነት እንዲሰፍን በር እንደሚከፍት ታምኖበታል።