በእሳት አደጋ 76 ዜጎቿን ያጣችው ቱርክ ብሄራዊ የሀዘን ቀን አወጀች
በምዕራባዊ ቱርክ በሚገኘው ግራንድ ካርታል ሆቴል ላይ ከደረሰው የእሳት ቃጠሎ ጋር በተያያዘ ዘጠኝ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል
ባለ12 ፎቁ ሆቴል 238 ሰዎችን በማስተናገድ ላይ እያለ ነው በእሳት የተያያዘው
በእሳት አደጋ 76 ዜጎቿን ያጣችው ቱርክ ዛሬ ጥቅምት 14 2017 ብሄራዊ የሀዘን ቀን እንዲሆን አውጃለች።
ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን በአሰቃቂው አደጋ ህይወታቸው ላለፈ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተው እለቱ ብሄራዊ የሀዘን ቀን እንዲሆን አውጀዋል።
በምዕራባዊ ቱርክ የጎብኝዎች መዳረሻ በሆነው ቦሉ ተራሮች በሚገኘው ግራንድ ካርታል ሆቴል በደረሰው አደጋ የሟቾች ቁጥር 76 የደረሰ ሲሆን፥ ከ50 ሰዎች በላይ ቆስለዋል።
የ45ቱ ሟቾች አስከሬን ለቤተሰቦቻቸው መተላለፉን ያስታወቁት የቱርክ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር አሊ የርሊካያ፥ የቀሪዎቹን ሟቾች ማንነት ለመለየት ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ የሆቴሉን ባለቤት ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ነው የተናገሩት።
የግራንድ ካርታል ሆቴል በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ በአደጋው ከፍተኛ ሀዘን እንደተሰማው ገልጾ ለተጀመረው ምርመራ ትብብር እንደሚያደርግ አስታውቋል።
ባለ12 ፎቁ ሆቴል አደጋው ሲደርስ 238 የተመዘገቡ እንግዶችን ሲያስተናግድ ነበር ተብሏል።
የአደጋው መንስኤ እስካሁን በይፋ አልተገለጸም። የቦሉ ግዛት አስተዳዳሪ አቡላዚዝ አይዲን የእሳት አደጋው አራተኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው የምግብ ማብሰያ ክፍል መቀስቀሱን ተናግረዋል።
ከአራተኛ ፎቅ የተነሳው እሳት ወደላይኛዎቹ ክፍሎች ተሸጋግሮ ከባድ ጉዳት ሲያደርስ ምንም አይነት የአደጋ ጊዜ ማሳወቂያ (አላርም) አለመጮሁም በሆቴሉ ላይ ወቀሳ አስነስቷል።
ከአደጋው የተረፉ ሰዎች በጭስ ታፍነው ራሳቸውን ለማዳን ያደረጉት ጥረት እጅግ አስፈሪ እንደነበር ተናግረዋል።
እሳት ለማምለጥ ከፎቅ ላይ የተወረወሩ ሁለት ሰዎች ህይወታቸው ማለፉንም ሬውተርስ ዘግቧል።
የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር 12 ስአታት ወስዷል የተባለ ሲሆን፥ በአካባቢው ያለው ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በስፍራው እስኪደርሱ በጥቂቱ አንድ ስአት እንዲወስድባቸው ማድረጉ ተገልጿል።
በ2024 በቱሪዝም ሚኒስቴር ባለሙያዎች ፍተሻ የተደረገበት ሆቴል ከእሳት አደጋ ጋር በተያያዘ ምንም አይነት የደህንነት ስጋት የለበትም ቢባልም ትናንት የደረሰው አደጋ ጥያቄ አስነስቷል።
የቱርክ ፍትህ ሚኒስቴር የ76 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው አደጋ መንስኤ ተመርምሮ ጥፋተኞች ተጠያቂ እንዲሆኑ ምርመራ መጀመሩን ይፋ አድርጓል።