በኬንያ ምርጫ 22 ሚሊዮን ህዝብ ድምጽ ይሰጣል ተብሏል
22 ሚሊዮን ኬንያዊያን ድምጽ እንደሚሰጡበት የሚጠበቀው የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሊካሄድ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ይቀራሉ።
በዚህ ምርጫ ላይ ላለፉት አራት ተመሳሳይ ምርጫዎች ተሳትፈው ሽንፈትን ያስተናገዱት የ 71 አመቱ ራይላ ኦዲንጋን ጨምሮ አራት እጩዎች ይወዳደሩበታል።
ይህ በዚህ እንዳለ ግን ኬንያን ላለፉት 10 ዓመታት በፕሬዝዳንትነት የመሩት ኡህሩ ኬንያታ የሽኝት ፕሮግራም እየተደረገላቸው ይገኛል።
ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ኡህሩ ኬንያታ ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ ለኬንያ የሰሩት ስራዎች እና ያላሳኳቸው እቅዶች መኖራቸውን ሮይተርስ በትንታኔው አስነብቧል።
ፕሬዝዳንት ኬንያታ ወደ ስልጣን ሲመጡ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከአፍሪካ በ13ኛ ደረጃ ይገኝ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ኬንያ ስድስተኛው ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ መሆን ችላለች።
የኬንያ የትራንስፖርት መሰረተ ልማቶች ከአፍሪካ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኝ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ዘመናዊ የባቡር ትራንስፖርት እና የገቢና ወጪ ንግድ የሚከናወንባቸው መሰረተ ልማቶች እንዳሏት ዘገባው አክሏል።
ይሁንና የኬንያ ውጭ ሀገራት ብድር መጠን ፕሬዝዳንት ኬንያታ ወደ ስልጣን ሲመጡ ሁለት ትሪሊዮን ሽልንግ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ወደ ዘጠኝ ትሪሊዮን ሽልንግ ወይም የሀገሪቱን ዓመታዊ ምርት መጠን 67 በመቶ ደርሷል ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ኬንያታ በአስር ዓመት የስልጣን ቆይታቸው ከቻይና ብቻ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር የተበደሩ ሲሆን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ ኬንያን ከፍተኛ የብድር ጫና ካለባቸው ሀገራት ተርታ አካቷታል።
አዲሱ ተመራጭ ፕሬዝዳንት የኬንያ ከፍተኛ የብድር ጫና፣ ከአራት ሚሊዮን በላይ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን መርዳት፣ ከፍተኛ የስራ አጥ ቁጥር እና በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የሚደርሰው የዋጋ ግሽበት ዋነኛ ፈተናዎቹ እንደሚሆኑ ተገልጿል።