የሳኡዲው ልዑል አልጋ ወራሽ ቢን ሳልማን ግሪክ እና ፈረንሳይን ለመጎብኘት ወደ አውሮፓ አቀኑ
ልዑሉ በአውሮፓ ምድር ጉብኝት ሲያደርጉ ከአከራካሪው የጀማል ኻሾጊ ግድያ በኋላ የመጀመሪያው ነው ተብሏል
የግሪክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ንጉስ ቢን ሳልማን ከጠ/ሚኒስትር ሚትሶታኪስ ጋር ይመክራሉ ብሏል
የሳኡዲ አረቢያ ልዑል ልዑል አልጋ ሞሀመድ ቢን ሳልማን በግሪክና ፈረንሳይ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ወደ አውሮፓ አቀኑ፡፡
የሳኡዲ አረቢያ ልዑል በአውሮፓ ምድር ጉብኝት ሲያደርጉ ከአከራካሪው የጀማል ኻሾጊ ግድያ በኋላ የመጀመሪያው መሆኑም የሳኡዲ የመንግስት የዜና ወኪል ኤስፒኤ ዘግቧል።
ልዑል አልጋ ወራሹ ለመጨረሻ ጊዜ ከመካከለኛው ምስራቅ ውጪ ጉብኝት ያደረጉት እንደፈረንጆቹ በ2019 በጃፓን ተዘጋጅቶ በነበረው የቡድን-20 ጉባኤ ለመሳተፍ ነበር።
የግሪክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ልዑል አልጋወራሹ ሞሀመድ ቢን ሳልማን ከጠቅላይ ሚኒስትር ኪሪያኮስ ሚትሶታኪስ ጋር እንደሚገናኙ አስታውቋል።
ሮይተርስ ከዲፕሎማቲክ ምንጮች አገኘሁት ብሎ እንደዘገበው ከሆነ ሁለቱም ሀገራት በሃይል፣ በወታደራዊ ትብብር እና የባህር ውስጥ የመረጃ ኬብል ዝርጋት እና ሌሎችም አንኳር ጉዳዮች ላይ በመመካከርና ከስምምነት በመድረስ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው ያጠናክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከግሪኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚትሶታኪስ በተጨማሪ ልዑል አልጋ ወራሹ አሁን የሚጎበኟት ሌላኛዋ ሀገር ፈረንሳይን የሚመሩት ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ባለፈው አመት እንዲሁም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ወደ ሪያድ መሄዳቸው ይታወሳል።