በሻምፒየንስ ሊጉ ግማሽ ፍጻሜ ለመግባት የተሻለ ግምት የተሰጣቸውክለቦች የትኞቹ ናቸው?
ትናንት ምሽት በተካሄዱ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ባርሴሎና እና አትሌቲኮ ማድሪድ አሸንፈዋል
የሻምፒዮንስ ሊጉ የሩብ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታዎች በቀጣዩ ሳምንት ይካሄዳሉ
የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ትናንት ምሽት ሲካሄዱ ባርሴሎና እን አትሌቲኮ ማድሪድ አሸንፈዋል።
በፓርክ ደ ፕሪንስ የካታላኑን ባርሴሎና ያስተናገደው ፒኤስጂ 3 ለ 2 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።
በቀድሞ ኮከቡ ዣቪ ሄርናንዴዝ የሚሰለጥነው ባርሴሎና በብራዚላዊው ራፊንሃ የ37 ደቂቃ ጎል ቀዳሚ ጎል እየመራ ለእረፍት ወጥቷል።
ከእረፍት መልስ በ48ኛው ደቂቃ በኦስማን ዴምቤሌ ጎል አቻ የሆነው ፒኤስጂ፥ ከሶስት ደቂቃ በኋላ በቪቲንሃ ሁለተኛዋን ጎል አስቆጥሮ ወደ መሪነት መመለስ ችሎ ነበር።
የአምስት ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ባለቤቱ ባርሴሎና፥ በራፊንሃ ሁለተኛ ጎል አቻ ሆኖ በአንድሬስ ክሪስተን የ71 ደቂቃ ጎል ወሳኝ ድል አስመዝግቧል።
በጫና ውስጥ ያለው ዣቪ በፈረንሳዩ ቡድን እንደሚሸነፍ ቢጠበቅም የተለየ ታክቲክ ይዞ በመግባት የሊዩስ ኤነሪኬን ቡድን ፈትኖታል።
በሌላ የሻምፒይንስ ሊጉ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ አትሌቲኮ ማድሪድ በሜትሮፖሊታኖ ስታዲየም ቦርሺያ ዶርትሙንድን ያስተናገደው አትሌቲኮ ማድሪድ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
ለዲያጎ ሲሞኒ ቡድን ሮድሪጎ ደ ፖል እና ሳሙኤል ዲያስ ሊኖ ጎሎቹን አስቆጥረዋል።
የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ያሳየው ቦርሺያ ዶርትሙንድ የሚያስቆጩ የጎል ሙከራዎችን አድርጎ በሰባስቲያን ሀለር የ81ኛ ደቂቃ ጎል በባዶ ከመሸነፍ ድኗል።
በሻምፒዮንስ ሊጉ ግማሽ ፍጻሜ ለመግባት ማን የተሻል እድል አለው?
ከትናንት በስቲያ የተደረጉት የአርሰናልና ባየርሙኒክ፤ የሪያል ማድሪድና ማንቸስተር ሲቲ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ነው የተጠናቀቁት።
በሻምፒዮንስ ሊጉ ከሜዳ ውጭ የሚቆጠር ጎል (አዌይ ጎል ህግ) በ2021 መሻሩ እንጂ ሁለቱም ግጥሚያዎች ድራማዊ ክስተት ያስተናግዱ ነበር።
በሻምፒዮንስ ሊጉ ከ14 አመት በኋላ ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀሉት መድፈኞቹ በቀጣዩ ሳምንት ረቡዕ በአሊያንዝ አሬና የሚያደርጉትን የመልስ ጨዋታ አሸንፈው ግማሽ ፍጻሜ ለመድረስ ይፋለማሉ።
የመልስ ጨዋታውን በኢትሃድ የሚያደርገው ማንቸስተር ሲቲ በአንጻሩ በጠባብ የጎል ልዩነት አሸንፎ ግማሽ ፍጻሜ ለመግባት የተሻለ ግምት ተሰጥቶታል።
የካታላኑ ክለብ ባርሴሎናም በፓርክ ደ ፕሪንስ ፒኤስጂን ማሸነፉ በቀጣዩ ሳምንት ማክሰኞ የመልስ ጨዋታውን በሜዳው ከማድረጉ ጋር ተዳምሮ ለዣቪ ቡድን የተሻለ ግምት እንዲሰጥ አድርጓል።
ሌላኛው የስፔን ቡድን አትሌቲክ ማድሪድ ማክሰኞ ቦርሺያ ዶርትሙንድን የሚገጥመው ከሜዳው ውጭ ቢሆንም ግማሽ ፍጻሜውን እንደሚቀላቀል የበርካቶች ግምት ነው።