ደቡብ አፍሪካዊው የእግር ኳስ ተጫዋች በመኪና ዘራፊዎች በተተኮሰበት ጥይት ህይወቱ አለፈ
የ24 ዓመቱ ሉክ ፍሉርስ የካይዘር ቼፍስ የእግር ኳስ ክለብ ተጫዋች ነበር
በ2021 የቶኪዮ ኦሎምፒካ ላይም ከደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድን ጋር ተሰልፎ ለሀገሩ ተጫውቷል
ደቡብ አፍሪካዊው የእግር ኳስ ተጫዋች ሉክ ፍሉርስ በመኪና ዘራፊዎች በተተኮሰበት ጥይት ህይወቱ ማለፉን የሀገሪቱ ፖሊስ አስታውቋል።
የ24 ዓመቱ ሉክ ፍሉርስ የተገደለው ባሳለፍነው ረቡዕ ምሽት በጆሃንስበርግ በሚገኝ ነዳጅ ማደያ ውስጥ በተተኮሰበት ጥይት መሆኑንም ነው ፖሊስ የገለጸው።
የ24 አመቱ የካይዘር ቺፍስ ኮከብ በነዳጅ ማደያው ውስጥ ነዳጅ ለመቅዳት በመጠባበቅ ላይ እያለ ማንነታቸው ባልታወቁ መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች ከመኪናው እንዲወርድ አድርገው እንደተኮሱበትም ታውቋል።
ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አንዱ ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ የፍሉርስን መኪና ይዞ ከቦታው መሸሹ ተዘግቧል።
በደቡብ አፍሪካ ታዋቂ ከሆኑ የእግር ኳስ ክለቦች አንዱ የሆነው እና የ12 ጊዜ የሊግ ሻምፒዮኑ ካይዘር ቺፍስ የተጫዋቹን ህልፈት "አሳዛኝ" ሲል ገልጿል።
የደቡብ አፍሪካ ስፖርት ሚኒስትር ዚዚ ኮድዋ "በአመፅ ወንጀል የእግር ኳስ ተጫዋቹ ህይወት በአጭር በመቀጨቱ አዝኛለሁ" ብለዋል።
በተከላካይ ስፍራ ላይ የሚጫወተው የ24 ዓመቱ ሉክ ፍሉርስ ካይዘር ቺፍስ የአግር ኳስ ክለብን የተቀላቀለው ባሳለፍነው ዓመት ሲሆን፤ ከዚያ ቀደም ብሎ ለሱፐር ስፖርት ዩናትድ ይጫወት ነበር።
ሉክ ፍሉርስ በ2021 የቶኪዮ ኦሎምፒካ ላይም ከደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድን ጋር ተሰልፎ ለሀገሩ ተጫውቷል።
ከዚህ ቀደም በዋናው የወንዶች ብሄራዊ ቡድን ውስጥ ተሰልፎ ያልተጫወተው ሉክ ፍሉርስ፤ ለዚህም እየተቃረበ እንደነበረ ነው የተገለጸው።
የሉክ ፍሉርስ የእግር ኳስ ህይወት የተጀመረው በፈረንጆቹ 2013 ሲሆን፤ የእግር ኳስን ዓለም የተቀላቀለውም በኡቡንቱ ኬፕ ታውን አካዳሚ እንደሆነ የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ዘግቧል።