የስፔናውያኑ አሰልጣኞች የሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ትንቅንቅ፤ ዣቪ ከኤነሪኬ
ፒኤስጂ በፓርክ ደ ፕሪንስ የገጠመውን ሽንፈት ቀልብሶ ግማሽ ፍጻሜውን ለመቀላቀል ባርሴሎናን ይገጥማል
አትሌቲኮ ማድሪድ ከጀርመኑ ቦርሺይ ዶርትሙድ የሚያደርገው ጨዋታም ይጠበቃል
የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት ይደረጋሉ።
የፈረንሳዩ ፒኤስጂ በሜዳው የደረሰበትን የ3 ለ 2 ሽንፈት ቀልብሶ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለመግባት ባርሴሎናን ይገጥማል።
ፒኤስጂ በመጀመሪያ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ተሸንፎ በመልሱ አሸንፎ ግማሽ ፍጻሜ ገብቶ ግን አያውቅም።
የፈረንሳዩ ቡድን አስልጣኝ ልዊስ ኤነሪኬ ይህን ታሪክ ቀልብሰውን ዛሬ ባርሴሎናን አሸንፈን ታሪክ እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።
ከባርሴሎና ጋር በ2014/15 የውድድር አመት የሶስትዮሽ ዋንጫን ያሳኩት ኤነሪኬ፥ተጫዋቾቻቸው “ከግል ፍላጎት የወጡና ለጋራ አላማ የቆሙ” መሆናቸው የቀድሞ ክለባቸውን ለማሸነፍ እንደሚያበቃቸው ተማምነዋል።
ባርሴሎና በ2017 ፒኤስጂን በደርሶመልስ 6 ለ 1 ሲያሸንፍ የክታላኑ ክለብ አሰልጣኝ የነበሩት ልዊስ ኤነሪኬ ታሪክ የማይለወጥበት ምንም ምክንያት የለም ብለዋል።
ባርሴሎና እና ፒኤስጂ በአውሮፓ መድረክ 14 ጊዜ ተገናኝተው ባርሴሎና ስድስት ጊዜ ሲያሸንፍ ፒኤስጂ አራት ጊዜ ረቷል።
ልዊስ ኤነሪኬ ባርሴሎናን የተረከቡበት አመት የአሁኑ የባርሴሎና አሰልጣኝ ዣቪ ሄርናንዴዝ በካምፕ ኑ የመጨረሻ አመት ቆይታው ማድረጉ ይታወሳል።
በአሰልጣኝነት እና ተጫዋችነት ሶስት ዋንጫዎችን ያሳኩት ኤነሪኬ እና ዣቪ ዛሬ ምሽት በተለያየ ክለብ ይፋለማሉ።
በሌላኛው የሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ የስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድ ወደ ሲግናል ኢድና ፓርክ በማቅናት ቦርሺያ ዶርትሙንድን ይገጥማል።
በሜዳው 2 ለ 1 ያሸነፈው የዲያጎ ሲሞኒው አትሌቲኮ ማድሪድ ግማሽ ፍጻሜውን እንደሚቀላቀል ይጠበቃል።
ባየርሙኒክ አርሰናልን፤ ማንቸስተር ሲቲ የስፔኑን ሪያል ማድሪድ በነገው እለት የሚያስተናግዱባቸው የሩብ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታዎች ተጠባቂ ናቸው።