ቻን የሀገር ውስጥ ሊግ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ነው
ሰባተኛው የቻን የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬም ቀጥሎ ሲካሄድ በምድብ ሶስት የተደለደሉት ሀገራት ይፋለማሉ።
ሞሮኮ ከሱዳን ምሽት 1 ስአት ፤ ማዳጋስካር ከጋና ደግሞ ምሽት 4 ስአት ላይ ይገናኛሉ።
በኳታር የአለም ዋንጫ አራተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ሞሮኮ በውጭ ሀገራት ሊጎች ከሚጫወቱት ተጫዋቾች ውጭ ከፍተኛ ሞራል ይዛ ሱዳንን ትገጥማለች።
ከአልጀሪያ ጋር ባለው የፖለቲካ ባላንጣነት የአትላስ አናብስቱ የቻን ተሳትፎ ሲያነጋግር ቢቆይም ዛሬ በሞሃመድ ሃሞላዊ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ከዚሁ ምድብ ሰፊ የማሸነፍ ግምት የተሰጣት ጋናም ማዳጋስካርን የምትገጥምበት ጨዋታ ይጠበቃል።
የቻን የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዎች ነገም ሲቀጥሉ ማሊ ከአንጎላ፤ ካሜሮን ከኮንጎ ብራዛቪል ይጫወታሉ።
በሀገር ውስጥ ሊጎች ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾች የሚሳተፉበት የቻን የአፍሪካ ዋንጫ ከትናንት በስቲያ ሲጀመር ሊቢያን የገጠመችው አስተናጇ አልጀሪያ በአይመን ማሂሎስ ብቸኛ ጎል ማሸነፏ ይታወሳል።
በዚሁ ምድብ የምትገኘው ኢትዮጵያ ከሞዛምቢክ ያደረገችው ጨዋታ ደግሞ ያለግብ ተጠናቋል።
በዚህም ምድቡን አልጀሪያ በሶስት ነጥብ እየመራች ነው፤ ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ በተመሳሳይ አንድ ነጥብ ይከተላሉ።
ምድብ ሁለትን ደግሞ ኮቲዲቯር 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ያሸነፈችው ሴኔጋል እየመራች ነው።
የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ከነገ በስቲያ ሲደረጉ ኢትዮጵያ አስተናጋጇን ሀገር አልጀሪያ ትገጥማለች።