ጽሁፍን ወደ ቪዲዮ ምስል የሚቀይረው ቻትጂፒቲ 4
አዲሱ የቻትጂፒቲ ማሻሻያ ከጽሁፍ ምላሽ ባሻገር የምንሰጠውን ጽሁፍ ወደ ድምጽ እና ቪዲዮ መለወጥ ይችላል ተብሏል
በህዳር ወር 2022 በይፋ የተዋወቀው ቻትጂፒቲ ተቀባይነቱ በፍጥነት እያደገ ይገኛል
የአሜሪካው ኦፕን አይ ኩባንያ ንብረት የሆነው ቻትጂፒቲ በዚህ ሳምንት በአዲስ ማሻሻያ እንደሚመጣ ይፋ አድርጓል።
ኩባንያው ጽሁፍን ወደተንቀሳቃሽ ምስል መቀየር የሚችል “ቻትጂፒቲ 4” የተሰኘ ቻትቦት ነው አገልግሎት አስጀምራለው ያለው።
ለማንኛውም አይነት ጥያቄ እንደሰው ልጅ ፈጣን የሆነ ምላሽ በመስጠት በአጭር ጊዜ ተቀባይነቱ ያደገው ቻትጂፒቲ፥ በመጪው ሃሙስ ይፋ የሚያደርገው ቻትጂፒቲ 4 ከጽሁፍ ምላሽ የተሻገረ “መልቲሞዳል” መልስን ያቀርባል ተብሏል።
ቻትጂፒቲ 4 በሚሊየን የሚቆጠሩ ምስሎች እና ድምጾች ጋር በሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አማካኝነት ተዋውቋል።
በዚህም የሰጠነውን ጽሁፍ ወደ ድምጽ፣ ቪዲዮ እና ፎቶ ለውጦ የመስጠት አቅም አለው ነው ያለው ማይክሮሶፍት።
በህዳር ወር 2022 የተለቀቀው ቻትጂፒቲ 3.5 ተጠይቆ አላውቀውም የሚለው ጉዳይ የለም፤ ግጥም ጽፎ ሙዚቀኞችንም ማስመሰል ይችላል።
የቢዝነስ ፕሮፖዛል ለመጻፍም ሆነ የምስጋና ደብዳቤ ለማዘጋጀት ሰከንዶች የሚበቁት ቻትጂፒቲ ፥ ሀሙስ ይፋ የሚያደርገው አዲስ ማሻሻያ የደንበኞቹን ቁጥር ይበልጥ ከፍ እንደሚያደርግለት ይታመናል።
ቻትጂፒቲ ለአንዳንድ ጥያቄዎች የሰጠው ምላሽ መነጋገሪያ ቢያደርገውም በየጊዜው በሚያደርገው ማሻሻያ ችግሮቹን እየቀረፈ እንደ ጎግል ላሉ ኩባንያዎች ብርቱ ፈተና እንደሚሆን ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ጽሁፍን ወደ ቪዲዮ የሚለውጠው ቻትጂፒት 4 ፌስቡክ ባለፈው የፈረንጆቹ አመት መስከረም ወር ላይ ይፋ ካደረገው “ሜክ ኤ ቪዲዮ” የተሰኘ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር ይመሳሰላል ተብሏል።
በአጭር ጊዜ በርካታ ተጠቃሚዎችን (ከ100 ሚሊየን በላይ) በማፍራት ክብረወሰን የያዘው ቻትጂፒቲ ከማይክሮሶፍት ጋር በመተባበር ቢንግ ላይ አገልግሎቱን ማስጀመሩ ጎግልን “ባርድ” የተሰኘ ቻትቦት እንዲከፍት ማድረጉ የሚታወስ ነው።