ጎግል የዶክተሮችን የእጅ ጽሁፍ የሚያነብ ቴክኖሎጂ ፈጥሬያለሁ አለ
በርካታ ዶክተሮች በመድሃኒት ማዘዣዎች ላይ የሚጽፉት ጽሁፍ ታካሚዎች ለማንበብ ሲቸገሩ ይስተዋላል
ጎግል የዶክተሮችን የእጅ ጽሁፍ መተርጎም የሚችል መተግበሪያ ነው የሰራው
የበርካታ ዶክተሮች በመድሃኒት ማዘዣዎች ላይ የሚጽፉት የእጅ ጽሁፎችን ማንበብ አስቸጋሪ መሆኑ ይታወቃል።
የዶክተሮችን የእጅ ጽሁፍ ማንበብ ለፋርማሲዎች ብቻ የተፈቀደ እስኪመስል ድረስ በርካቶች የሚቸገሩበት ሲሆን፤ በርካታ የቴክኖሎጂ ኩባያዎችም በዚህ ላይ ሲሰሩ መቆየታቸው ይታወቃል።
ጎግል ግን ይህንን የማይነበብ የዶክተሮች የእጅ ጽሁፍ የሚተረጉም አዲስ ቴክኖሎጂ ይዞ መምጣቱን ከሰሞኑ ይፋ አደርጓል።
ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጎግል በህንድ ባደረገው ዓመታዊ ጉባዔ ላይ እንዳስታወቀው የዶክተሮችን የእጅ ጽሁፍ ማንበብ የሚችል ቴክኖሎጂ ላይ ከፋርማሲ ባለሙያዎች ጋር እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
በአሁኑ ሰዓት በሙከራ ደረጃ ያለው አዲሱ የጎግል ቴክኖሎጂ ለህዝብ ይፋ ያልተደረገ ሲሆን፤ ለህዝብ ሲለቀቅ ግን ታካሚዎች የተሰጣቸውን የመድሃኒት ማዘዣ ፎቶ በማሳት ብቻ መረዳት ይችላሉ ተብሏል።
ፎቶ ግራፉ አንድ ጊዜ ስልካችን ላይ ከገባ በኋላ መተግበሪያው ፎቶው ላይ ያለውነ ጽሁፍ በማንበብ ምንነቱን የሚነግረን ይሆናል።
"ይህ በእጅ የተጻፉ የሕክምና ሰነዶችን ዲጂታል ለማድረግ እንደ አጋዥ ቴክኖሎጂ ሆኖ ያገለግላል” ያለው ጎግል “ነገር ግን በዚህ ቴክኖሎጂ በሚሰጠው ውጤት ላይ ብቻ ውሳኔ አይደረግም" ሲል ገልጿል።