ኤምሬትስ ያለሰው ንክኪ የስራ ውልን የሚጨርስ ቴክኖሎጂ ስራ ላይ አዋለች
ቴክኖሎጂው ሁለት ቀን ይወስድ የነበረውን በ30 ደቂቃ ብቻ ለማጠናቀቅ ያስችላል ተብሏል
ሀገሪቱ በ2031 የአለማችን ቀዳሚዋ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ተጠቃሚ ለመሆን እየሰራች ነው
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ያለምንም የሰው ልጅ ጣልቃ ገብነት የስራ ውሎችን መፈራረም የሚያስችል ቴክኖሎጂን ወደ ስራ አስገብታለች።
የሀገሪቱ የሰው ሀብት ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፥ ቴክኖሎጂው በጥቂቱ ሁለት ቀናት ይወስድ የነበረውን አዲስ የስራ ውል መፈራረምም ሆነ ማደስ በ30 ደቂቃ መጨረስ የሚያስችል ነው።
ከሰው ንክኪ ነጻ የሆነው ስርአት ስራ በጀመረ በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ ከ35 ሺህ በላይ የስራ ውሎች በዚሁ ቴክኖሎጂ ተፈርመዋል ነው ያለው ሚኒስቴሩ።
ሁለቱ (ስራ ቀጣሪውና ሰራተኛው) ፊርማቸውን እንዲያኖሩ የሚያደርገው የሰው ሰራሽ አስተውሎት፥ የተዋዋዮቹን ፎቶ በማመሳከር ብቻ ከየትም ሆነው ስምምነቱን እንዲፈራረሙ ያስችላል።
ይህም ጊዜና ሃብትን ከብክነት እንደሚታደግና በሰው ልጅ የሚፈጸሙ ህጸጾችን እንደሚያስወግድ ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።
ደንበኞች “ናፌስ” በተሰኘው በሚኒስቴሩ መተግበሪያ አገልግሎቱን ማግኘት ይችላሉ ተብሏል።
በዚሁ መተግበሪያ ከ100 በላይ አገልግሎቶችን በሞባይል ስልኮችና ኮምፒውተሮች ያለምንም የስአት ገደብ ማግኘት እንደሚቻልም ነው ሚኒስቴሩ ይፋ ያደረገው።
በፈረንጆቹ 2031 በሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) የአለማችን ፈር ቀዳጅ ሀገር ለመሆን እየሰራች ያለችው አቡ ዳቢ፥ ከ2017 ወዲህ ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው።
በሰው ሰራሽ አስተውሎት በርካታ የመንግስት ተቋማት አገልግሎቶችን ከሰዎች ጣልቃ ገብነት ነጻ ለማድረግ፣ የስራ ውጤታማነትን ለመጨመርና ጥሩ የስራ ከባቢን ለመፍጠር የጀመረችው ስራም ውጤት ማሳየት ጀምሯል።
ሀገሪቱን በ100ኛ አመት የምስረታ በዓሏ (2071) በሁሉም ዘርፎች ፈር ቀዳጅ በማድረጉ ሂደት የዲጂታል ዘርፉን የማዘመኑ ስራ መሰረታዊ ተደርጎ እየተሰራበት ነው።