ኢንዱስትሪዎች ጥቂት የታዳሽ ሀይል አማራጮች ብቻ እንዳሏቸው ተገለጸ
የአማራጮች ማነስ ከባድ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ታዳሽ ሀይል ለመውሰድ እየተደረገ ላለው ጥረት ዋነኛ ፈተና ሆኗል ተብሏል
ሮንዶ ሲስተም የተሰኘው ኩባንያ ለከባድ ኢንዱስትሪዎች የታዳሽ ሀይል አማራጭ ባትሪ ለማምረት በሙከራ ላይ መሆኑን አስታውቋል
ኢንዱስትሪዎች ጥቂት የታዳሽ ሀይል አማራጮች ብቻ እንዳሏቸው ተገለጸ።
የዓየር ንብረት ለውጥ ዓለማችንን ከባድ ዋጋ እያስከፈላት ነው የተባለ ሲሆን ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ኢንዱስትሪዎች የታዳሽ ሀይል እንዲጠቀሙ የቀረቡላቸው አማራጮች ጥቂት በመሆናቸው ነው ተብሏል።
በተለይም የብረታ ብረት እና የሲሚንቶ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለረጅም ሰዓት ሀይል የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ይህ መሆኑ ደግሞ የታዳሽ ሀይልን እንደ አማራጭ እንዳይጠቀሙ አቅርቦቱ ባለመኖሩ እንደሆነ ተገልጿል።
ለአየር ንብረት ተስማሚ የሆኑ የታዳሽ ሀይል አማራጮች ደግሞ ውድ እና እንደ ልብ አለመገኘታቸው ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ የካርበን ጋዝ የሚለቁ የሀይል አማራጮችን ለመጠቀም መገደዳቸው ይገለጻል።
ከከባድ ኢንዱስትሪዎች የሚለቀቁ በካይ ጋዞች መጠን ከጠቅላላው የ25 በመቶ ድርሻ አላቸው የተባለ ሲሆን ለዚህ ዘርፍ የታዳሽ ሀይልን እንደ አማራጭ መጠቀም የሚችሉባቸው ቴክኖሎጂዎች ቢኖሩ ለጤናማ የአየር ንብረት አስተዋጽኦው ብዙ ይሆናል።
ይህን አማራጭ ለመተግበር ብዙ የዓለማችን ኩባንያዎች ፍላጎት ቢኖራቸውም ጥረት የጀመሩት ግን ጥቂት ናቸው ተብሏል።
ከነዚህ መካከልም በአሜሪካ ካሊፎርኒያ የሚገኘው ሮንዶ ሲስተም የተረሰኘው ኩባንያ ሀይልን ማጠራቀም የሚችሉ ባትሪዎችን ለማምረት በሙከራ ላይ መሆኑ ተገልጿል።
ኩባንያው ሊያመርተው ያሰበው ባትሪ ቢያንስ ለአራት ሰዓት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ባትሪ እንደሆነ ተገልጿል።
ይህ ለከባድ ኢንዱስትሪዎች ታስቦ በሙከራ ላይ ያለው ባትሪ ቻርጅ በማድረግ መልሶ ጥቅም ላይ እንደሚውልም ተጠቅሷል።