ዲፒ ወርልድ በብራዚል ሳንቶስ ወደብ የታዳሽ ሃይል ሽግግር ጀምሯል
የዱባዩ ዲፒ ወርልድ በወደቡ የሚገኙ ሁሉም ክሬኖች በኤሌክትሪክ ሃይል እንዲሰሩ 15 ሚሊየን ዶላር በጅቷል
ኩባንያው የካርበን ልቀትን ለመቀነስ የሚያስችሉ የ500 ሚሊየን ዶላር ፕሮጀክቶች ይዟል
ከ70 በላይ ሀገራት በወደብ ተርሚናል ማስተዳደር እና ሎጅስቲክን በማቀላጠፍ ስራ የተሰማራው የዱባዩ ዲፒ ወርልድ በ2040 ሙሉ በሙሉ የካርበን ልቀትን ዜሮ ለማድረስ እየሰራ ነው።
ዲፒ ወርልድ በብራዚል ሳንቶስ ወደብ ላይም የታዳሽ ሃይል ሽግግር እያደረገ መሆኑን ነው ያስታወቀው።
ኩባንያው 16 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር መድቦ በወደቡ የሚገኙ እቃ የሚጭኑ እና የሚያወርዱ ክሬኖች በኤሌክትሪክ ሃይል እንዲሰሩ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጿል።
በወደቡ የሚገኙ 26 ክሬኖች (በነዳጅ ይሰሩ የነብሩ) በ2024 ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ እንዲሰሩ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ነው በሳንቶስ ወደብ የዲፒ ወርልድ ስራ አስፈጻሚ ፋቢዮ ሴሰሪኖ የተናገሩት።
የታዳሽ ሃይል ሽግግሩ የወደቡን የነዳጅ ፍጆታ በ60 በመቶ እንደሚቀንሰው በመጥቀስም የአየር ብክለትን ከመቀነስ ባሻገር ከፍተኛ ወጪን እንደሚያድን አብራርተዋል።
የዲፒ ወርልድ የአለማቀፍ ፕሮጀክቶች ምክትል ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አል ሙአለም ከብራዚል ምክትል ፕሬዝዳንት ጀራልዶ አልኩመን ጋር በዚህ ሳምንት በብራዚሊያ ተወያይተዋል።
በዚሁ ወቅትም ዲፒ ወርልድ በሳንቶስ ወደብ በ35 ሚሊየን ዶላር ስለሚጀምረው የማስፋፊያ ፕሮጀክት እና የታዳሽ ሃይል ሽግግሩ ዙሪያ መክረዋል።
ዲፒ ወርልድ ከ75 በላይ ሀገራት ባሉት የወደብ መሰረተ ልማቶች አሉት።
ኩባንያው የካርበን ልቀትን ለመቀነስና የታዳሽ ሃይልን ለማስፋፋት ለቀጣይ አምስት አመታት 500 ሚሊየን ዶላር በጀት መያዙን የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ሱልጣን አህመድ ቢን ሳሌም ተናግረዋል።
ዲፒ ወርልድ የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ እስካሁን በከወናቸው ተግባራትም በ2022 በ5 በመቶ የካርበን ልቀትን መቀነስ መቻሉን ነው የገለጹት።
በወደብ ውስጥ የሚከማቹ ቆሻሻዎችን ወደ ሃይል ምንጭነት እና የኢንዱስትሪ ግብአትነት በመለወጥ ረገድም ኩባንያው አበረታች ስራዎችን እያከናወነ መሆኑ ተጠቅሷል።