ሙዚቀኞች ፈጣን ስልተምት ያላቸው ስራዎቻቸውን እስከ ሰኔ 1 እንዲያስተካክሉ ታዘዋል ተብሏል
ቺቺኒያ ፈጣን ስልተ ምት ያላቸውን መዚቃዎች አገደች።
የሩሲያ አካል የሆነችው የቺቺኒያ ሪፐብሊክ ሁሉም ሙዚቃዎች ፍጥነታቸው “በደቂቃ ከ80 እስከ 118 ቢት” ብቻ ሊሆን ይገባል ብላለች።
የግዛቷ ባህል ሚኒስቴር አዲሱን የሙዚቃ ህግ በተመለከተ ከሙዚቀኞች ጋር መምከሩንም ሞስኮ ታይምስ አስነብቧል።
የሙዚቃ ምት ፍጥነትን የሚወስነው ህግ ከዘመናዊ የፖፕ ሙዚቃዎች እና ከበርካታ የምዕራባውያን የሙዚቃ ስልቶች ጋር ሲነጻጸር ዘገም ያለ መሆኑ ተገልጿል።
የቺቺኒያ ሪፐብሊክ አስተዳዳሪ ታምዛን ካድይሮቭ ለባህል ሚኒስትሩ ሙሳ ዳዳየቭ በጻፉት ትዕዛዝ መሰረት የወጣው ህግ “የቺቺኒያን ሙዚቃ ከማህበረሰቡ ስነልቦና ጋር ለማጣጣም” ያለመ ነው ተብሏል።
የባህል ሚኒስትሩ ሙሳ ዳዳየቭ “የሌሎችን የሙዚቃ ባህል በመዋስ በአደባባይ ማቀንቀን የተከለከለ ነው” ማለታቸውንም ሞስኮ ታይምስ በዘገባው አስፍሯል።
ሚኒስትሩ ከአርቲስቶች ጋር ባደረጉት ምክክር ሙዚቀኞች ፈጣን ስልተምት ያላቸው ስራዎቻቸውን እስከ ሰኔ 1 2024 በወጣው መስፈርት መሰረት አስተካክለው በድጋሚ እንዲሰሩ አዘዋል።
በመስፈርቱ መሰረት ፈጣን ስልተምት ያላቸው የሙዚቃ ስራዎቻቸውን የማያስተካክሉ አቀንቃኞች መድረክ ላይ እንዳይዘፍኑ ይታገዳሉ ነው የተባለው።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ያወጀችውን ጦርነት የደገፈችው ቺቺኒያ ምዕራባውያን በሙዚቃዎች የሚፈጥሩትን ተጽዕኖ በመቃወምም ትታወቃለች።
በቅርብ አመታት ውስጥም በርካታ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን የሚቃወሙ ሰልፎች ተካሂደውባታል።