ከዲሮቭ ከፈረንጆቹ 2007 ጀምሮ ቺቺኒያ ግዛትን በአስተዳዳሪነት እየመራ ይገኛል
የሩሲያዋ ቺቺኒያ መሪ ራምዛን ከዲሮቭ የራሱን ጦር ማቋቋም እንደሚፈልግ ተናገረ፡፡
ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ልዩ ዘመቻ ነው በሚል የተጀመረው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርቶታል፡፡
በሩሲያ ስር ጦር ከላኩ ክልሎች መካከል በራምዛን ከዲሮ የሚመራው ቺቺኒያ ግዛት ወታደሮች ዋነኞቹ ሲሆኑ ወደ ዩክሬን ገብተው እየተዋጉ ይገኛሉ ተብሏል፡፡
ከሩሲያው ቅጥረኛ ወታደሮች ወይም ዋግነር ግሩፕ ጎን ዩክሬንን ከሩሲያ ብሄራዊ ጦር ጋር እየተዋጉ ያሉት የቺቺኒያው ራምዛን ካዲሮ በቀጣይ የግል ወታደራዊ ቡድን ማቋቋም ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል፡፡
የዋግነር ጦር አባላት በዩክሬን ምድር እያደረጉት ባለው ጦርነት ድል እየተቀዳጁ ናቸው የሚለው ካዲሮቭ በቀጣይ አሁን የያዘውን ተልዕኮ ሲያጠናቅቅ የራሱን ቅጥረኛ ወታደራዊ ተቋም አቋቋማለሁ ማለቱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በቨግኒ ፕሪጎዚን የሚመራው የዋግነር ግሩፕ በዩክሬን አስደናቂ ድል እያስመዘገበ መሆኑን የጠቀሰው ካዲሮቭ የግል ቅጥረኛ ወታደራዊ ኩባንያ ማቋቋም ያስፈልጋል ማለቱ ተገልጿል፡፡
ራምዛን ካዲሮቭ የሩሲያ አንድ ግዛት የሆነችው ቺቺኒያ ግዛትን ከፈረንጆቹ 2007 ጀምሮ በአስተዳዳሪነት እየመራ ሲሆን የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የቅርብ ወዳጅ እንደሆኑም ይነገርላቸዋል፡፡
የዋግነሩ አለቃ ፕሪጎዚን እና ካዲሮቭ ከዩክሬን ጋር እየተካሄደ ባለው ጦርነት ከፍተኛ የጦር ሃላፊነት ካላቸው ሰዎች መካከል ዋነኞቹ ግለሰቦች ናቸው፡፡
በድርድር ቶሎ ይቋጫል የተባለው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በየጊዜው አዳዲስ ክስተቶችን እያስተናገደ የቀጠለ ሲሆን ምዕራባዊያን ሀገራት ለዩክሬን በየጊዜው የጦር መሳሪያ በመስጠት ላይ ናቸው፡፡
ሩሲያ በበኩሏ ለዩክሬን የሚሰጥ የጦር መሳሪያ ከአሜሪካ እና ኔቶ ጋር የቀጥታ ጦርነት እንዲጀመር ከማድረጉ ባለፈ ወደ ሶሰተኛው የዓለም ጦርነት ይወስዳል ስትል በማስጠንቀቅ ላይ ትገኛለች፡፡