የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አማጽያን በምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል ስትራቴጂያው ከተማ ተቆጣጠሩ
በሩዋንዳ የሚደገፉት ኤም 23 የተባሉት አማጺያን ጎማ ከተማን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል

በድንበር አቅራቢያ በሩዋንዳ እና በዲአር ኮንጎ ወታደሮች መካከል የተኩስ ልውውጥ መደረጉ ተገልጿል
በሩዋንዳ የሚደገፉት የዴሞክራቲክ ኮንጎ አማፂያን በምስራቃዊ ኮንጎ ትልቁን ከተማ መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ነዋሪዎች እየሸሹ ነው፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አማፂያኑ ለቀው እንዲወጡ ጥሪ ቢያቀርብም ከቅርብ ቀናት ወዲህ በተባባሰው ውጊያ አማጺያኑ የመንግስትን ሀይሎች በማስለቀቅ ጎማ ከተማን ተቆጣጥረዋል፡፡
ሰኞ ማለዳ በሩዋንዳ ድንበር ላይ ወደምትገኘው የሰሜን ኪቩ ግዛት ዋና ከተማ ወታደራዊ ዩኒፎርሞችን የለበሱ አማፂያን ከመግባታቸው በፊት ጎማ ከተማ አቅራቢያ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበር ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ከሩዋንዳ መንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት ያቋረጥው የዴሞክራቲ ኮንጎ መንግስት ከዋና ከተማዋ ኪንሻሳ 1500 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኝው ከተማ በአማጽያን እጅ መውደቋን አስተባብሏል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገው የዲፕሎማሲያዊ ድርድር ሙከራ አለመሳካቱን ተከትሎ ከኪጋሊ ጋር ግኙነቷን ያቋረጠችው ኮንጐ ባለሥልጣናት ሩዋንዳ ጦርነት አውጃለች ሲሉ ከሰዋል፡፡
ይህን ተከትሎም በሰሜናዊ ኪቩ ድንበር አቅራቢያ የኮንጎ እና የሩዋንዳ ወታደሮች የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
የኤም 23 አማፅያን በማዕድን በበለፀገው ቀጠና ውስጥ ላለፉት አስርተ ዓመታት በዘለቀው ግጭት ከሚሳተፉ 100 የሚጠጉ ታጣቂ ቡድኖች መካከል አንዱ ነው፡፡
ይህ ቡድን በ2012 የጎማ ከተማን ተቆጣጥሮ የነበረ ቢሆንም በአለም አቀፉ ማህበረሰብ በደረሰበት ከፍተኛ ጫና ከተማዋን ለቆ ወጥቶ ነበር፡፡
ቀጥሎም ከሩዋንዳ የሚደረግለትን ከፍተኛ ድጋፍ ተከትሎ ዳግም ይዞታዎቹን እጠናከሮ እንደሚገኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የኮንጎ መንግስት ይከሳሉ፡፡
ተንታኞች በቅርብ ቀናት ተባብሶ የቀጠለው ውጥረት ከ6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የተፈናቀሉበት የአለማችን ትልቁ የሰብአዊ ቀውሶች መገኛ የሆነውን ቀጠና የበለጠ መረጋጋትን እንደሚያሳጣ አስጠንቅቀዋል።
ከተፈናቃዮቹ መካከል ከሩዋንዳ ጋር የሚዋሰነው የሰሜን ኪቩ ህዝብ አንድ ሶስተኛውን እንደሚሸፍን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት አመልክቷል።
በጉዳዩ ላይ ትላንት ምሽት የተሰበሰበው የፀጥታው ምክር ቤት ኤም 23 ለዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሉዓላዊነት እና ግዛታዊ አንድነት ስጋት መሆኑን እንዲያቆም እና በግዛቱ ውስጥ የመሰረታቸውን ትይዩ አስተዳደሮች እንዲያፈርስ ጠይቋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሁለት አስርተ አመታት በፊት ያሰማራቸው እና 14 ሺህ የሚጠጉ የሰላም አስከባሪ ሀይሎች በስፍራው ያሉት ሲሆን ባለፉት ሳምንታት በተጠናከረው ውጊያ 13 አባላቶቹ እንደተገደሉበት አስታውቋል፡፡
ከሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ጨምሮ በአካባቢው በመንግስት ወታደሮች እና በአማጺኑ መካከል ሰፊ ውግያ መቀስቀሱን ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪዎች በብዛት ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል፡፡