ሀማስ ይለቀቃሉ ከተባሉት 33 የእስራኤል ታጋቾች ውስጥ የ25ቱን ስም ዝርዝር ለአደራዳሪዎቹ መስጠቱን አስታወቀ
ለ15 ወራት የዘለቀውን ጦርነት ያስቆመው የተኩስ አቁም ስምምነት መደረሱን ተከትሎ ታጋቾች በፍልስጤማውያን እስረኞች እየተለወጡ በመፈታት ላይ ናቸው

በተኩስ አቁም ስምምነት የመጀመሪያ ምዕራፍ 33 የእስራኤል ታጋቾች እንደሚለቀቁ እና 2000 ገዳማ ፍልስጤማውያን እስረኞች ከእስራኤል እስርቤቶች እንደሚለቀቁ ይጠበቃል
ሀማስ ይለቀቃሉ ከተባሉት 33 የእስራኤል ታጋቾች ውስጥ የ25ቱን ስም ዝርዝር ለአደራዳሪዎቹ መስጠቱን አስታወቀ።
የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ ከሁለት ሳምንት በፊት ከእስራኤል ጋር በደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት በፍልስጤማውያን እስረኞች ተለውጠው ይለቀቃሉ ከተባሉት 33 ታጋቾች ውስጥ የ25ቱን ስም ዝርዝር ለአደራዳሪዎቹ መስጠቱን ሮይተርስ የሀማስ ባለስልጣንን ጠቅሶ ዘግቧል።
ባለስልጣኑ በጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት አደራዳሪዎቹ በህይወት ያሉ የ25 ታጋቾችን ስም ዝርዝር ተቀብለዋል ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
መካከለኛው ምስራቅን ያመሰቃቀለዉንና ለ15 ወራት የዘለቀውን ጦርነት ያስቆመው የተኩስ አቁም ስምምነት መደረሱን ተከትሎ ታጋቾች በፍልስጤማውያን እስረኞች እየተለወጡ በመፈታት ላይ ናቸው።
የተኩስ አቁሙ ተግባራዊ በሆነበት የመጀመሪያው ቀን ሶስት ታጋቿች በ90 ፍልስጤማውያን እስረኞች ሲለወጡ፣ ባለፈው ቅዳሜ ደግሞ አራት ታጋች የእስራኤል ወታደሮች በ200 የፍልስጤም እስረኞች ተለውጠዋል።
ስምምነቱ ተግባራዊ መሆን በጀመረበት ቀን ሮሚ ጎኔን፣ ኢምሊ ደማሪና ዶሮን ስቴንብሬቸር የባሉ የእስራኤል ታጋቾች ተለቀዋል።
ባለፈው ቅዳሜ ደግሞ ሀማስ ጥቅምት 7፣2023 በደቡብ እስራኤል ድንበር ጥሶ ጥቃት በከፈተበት ወቅት ታግተው የተወሰዱት ካሪና አሪቭ፣ ዳኒኤላ ጊልባኦ፣ናአሜ ለቪይ እና ሊሪ አልባግ የተባሉ አራት ሴት የእስራኤል ወታደሮች ተለቀው ከቤተሰቦቻቸው ተቀላቅለዋል።
ለስድስት ሳምንት በሚቆየው የጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነት የመጀመሪያ ምዕራፍ 33 የእስራኤል ታጋቾች እንደሚለቀቁ እና 2000 ገዳማ ፍልስጤማውያን እስረኞች ከእስራኤል እስርቤቶች እንደሚለቀቁ ይጠበቃል።
በግብጽና ኳታር የተመራውና ሞቅ ቀዝቀዝ እያለ ለወራት በተካሄደው ድርድር የተደረሰው ተኩስ አቁም ስምምነት በህዳር 2023 ለአንድ ሳምንት ከቆየው ተኩስ ጋብ የማድረግ ስምምነት ወዲህ ውጊያውን ለመጀመሪያ ጊዜ አስቁሞታል።
በመጀመሪያው ዙር ሀማስ 33 ተሟጋቾችን በእስራኤል እስርቤቶች ታሰረው የሚገኙ በመቶዎች በሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ለመለወጥ ተስማምቷል። በሁለተኛው ዙር ሁለቱ ወገኞች የቀሩ ታጋቿች በሚለቀቁበትና የእስራኤል ጦር ለ15 ወራት በዘለቀው ጦርነት በአብዛኛው ከፈራረሰችው ከጋዛ በሚወጣበት ሁኔታ ይደራደራሉ።
ሀማስ በጥቅምት 7፣ 2023 በእስራኤል ላይ ጥቃት በመክፈት 1200 ሰዎችን መግደሉን እና 250 ሰዎችን አግቶ መወሰዱን ተከትሎ እስራኤል በከፈተችው ዘመቻ 47ሺ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።