የፑቲን አጋር የሆኑት የቤላሩሱ ፕሬዝደንት ሉካሸንኮ ምርጫ ማሸነፋቸውን አወጁ
በመጀመሪያ ደረጃ ውጤት መሰረት ከሌሎች አራት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህ ነው የሚባል ተቃውሞ ያልገጠማቸው ሉካሸንኮ 86.8 በመቶ ድምጽ በማግኘት አሸንፈዋል
ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" ሁለቱን ሀገራት የበለጠ እንዲቀራረቡ አድርጓቸዋል
የፑቲን አጋር የሆኑት የቤላሩሱ ፕሬዝደንት ሉካሸንኮ ምርጫ ማሸነፋቸውን አወጁ።
የቤላሩሱ ፕሬዝደንትና የሩሲያ አጋር ሉካሸንኮ በምዕራባውያን እውቅ የተነፈገውን ምርጫ ማሸነፋቸውን የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ባለስልጣናት በዛሬው እለት ማወጃቸውን ተከትሎ የ31 አመት የስልጣን ዘመናቸውን አራዝመዋል።
በመጀመሪያ ደረጃ ውጤት መሰረት ከሌሎች አራት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህ ነው የሚባል ተቃውሞ ያልገጠማቸው ሉካሸንኮ 86.8 በመቶ ድምጽ በማግኘት አሸንፈዋል።
ምዕራባውያን ፖለቲከኞች ነጻ ሚዲያ ባለመገኙቱ ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ አለመሆኑን እየገለጹ ናቸው።
"የቤላሩስ ህዝብ ምርጫ የለውም። ዲሞክራሲና ነጻነት ለሚፈልጉት መራራ ቀን ነው" ሲሉ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ባይሮቦክ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል። በስደት ላይ የሚገኙት የቤላሩስ ፖለቲከኛ ሲቪትላና ቲስካኖስካያ በቤላሩስ ኩባንያዎችና የሉካሸንኮ ተቃዋሚዎችን በመጨቆን በሚሳተፉ ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ እንዲጣልና ከሩሲያ ጋር እየተዋጋች ላለችው ዩክሬን የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንዲቀርብ ጥሪ አድርገዋል።
"ቤላሩስ በሉካሸንኮና ፑቲን ስር እስከሆነች ድረስ በአጠቃላይ የቀጠናው ሰላም እና ደህንነት ላይ ስጋት ይወድቃል" ብሏል።
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ካጃ ካላስና የማስፋፋት ኮሚሽን ማርታ ኮስ ባወጡት መግለጫ በውጭ ያሉ ፖለቲከኞችንና የሲቪል ማህበረስብ ድርጅቶችን ከመርዳት ባለፈ "ጥብቅና በአገዛዙ ላይ ያነጣጠረ እርምጃ" መውሰዱን ይቀጥላል ብለዋል።
ባለፈው እሁድ ስለታሰሩት ተቃዋሚዎቻቸው የተጠየቁት ፕሬዝደንት ሉካሸንኮ እጣፈንታቸውን "መርጠዋል" የሚል መልስ ስጥተዋል።"ስለምዕራባውያን አልጨነቅም" ብለዋል ሉካሸንኮ።
ሉካሸንኮ በስልጣን ዘመናቸው የሩሲያ የቅርብ አጋር በመሆኑን ዘጠኝ ሚሊዮን የሚሆነው የሀገሪቱ ህዝብ በጎረቤት እንዳይዋጥ እየተካለከሉ ከሩሲያ ርካሽ ነዳጅና ብድር ማግኘት ችለዋል።
ነገርግን ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" ሁለቱን ሀገራት የበለጠ እንዲቀራረቡ አድርጓቸዋል። ፕሬዝደንት ፑቲን ለመጀመሪያ ጊዜ ከሩሲያ ውጭ በቤላሩስ የታክቲክ ኑክሌር ጦር መሳሪያ ልከዋል።