ሮናልዶ 18 ጊዜ ምርመራ ቸድርጎ በሁሉም ቫይረሱ ተገኝቶበታል
ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከኮሮና ባለማገገሙ የዛሬው ጨዋታ ያመልጠዋል
ጁቬንቲዩስ ከባርሴሎና ጋር በሚያደርገው የሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ ከታላቅ ተቀናቃኙ ሊዮኔል ሜሲ ጋር ይገናኛል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በጨዋታው ዋዜማ ላይ ባደረገው ምርመራ ከኮሮና ቫይረስ አለማገገሙን ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡
የአምስት ጊዜ የባሎን ዶር አሸናፊው ሮናልዶ 18 ጊዜ ተመርምሮ በሁሉም ቫይረሱ ተገኝቶበታል፡፡
የ 35 ዓመቱ ፖርቱጋላዊ ለመጀመሪያ ጊዜ ኮቪድ -19 የተገኘበት ከሁለት ሳምንት በፊት በአውሮፓ ሀገራት ሊግ ለሀገሩ ሲጫወት ሲሆን የምርመራ ውጤቱን ተከትሎ ወደ ጣሊያን ከተመለሰ በኋላ ራሱን አግልሎ ይገኛል፡፡
በምድብ ሰባት የተደለደሉት ጁቬንቲዩስ እና ባርሴሎና ጨዋታቸውን ዛሬ ምሽት በቱሪን ያካሒዳሉ፡፡
በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ህግ መሰረት ሮናልዶ በጨዋታው ለመሳተፍ ከጨዋታው 24 ሰዓት በፊት ከቫይረሱ ነጻ መሆን ይጠበቅበት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ሊሆን አለመቻሉ ትናንት ፕሬዝዳንቱን ላሰናበተው እና በጥሩ አቋም ላይ ለማይገኘው ባርሴሎና መልካም የሚባል ዜና ነው፡፡