ቼልሲ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ባለድል ሆኗል
ጋርዲዮላ ይህን ዋንጫ ማሸነፍ አለማቻሉ ከክለቡ ጋር በሚኖረው ቀጣይነት ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ይጠበቃል
የቼልሲው ንጎሎ ካንቴ የጨዋታው ኮከብ ሆኗል
ሁለቱ የእንግሊዝ ክለቦች ማንችስተር ሲቲ እና ቼልሲ በተገናኙበት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ቼልሲ 1 ለ 0 በማሸነፍ ዋንጫውን አንስቷል።
በፖርቹጋሉ የፖርቶ ሜዳ በተካሔደው ጨዋታ ፣ በ42ኛው ደቂቃ ሀቬርዝ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል ሲቲን በመርታት ቼልሲ የአህጉሪቱን ታላቅ ዋንጫ በታሪኩ ለሁለተኛ ጊዜ አጣጥሟል።
ላምፓርድን በመተካት ጥር ወር ላይ ቼልሲን የተረከበው ቶማስ ቱሄል ከክለቡ ጋር በተወዳጁ ዋንጫ የመጀመሪያ ድሉን ሲያጣጥም ማንችስተር ሲቲ በአንጻሩ ለዘመናት የሚናፍቀውን ዋንጫ አሁንም በናፍቆት መጠበቅ ግድ ብሎታል።
የሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ፣ ክለቡ እንዲያሳካ የሚጠብቅበትን ይህን ዋንጫ ማሸነፍ አለማቻሉ ከክለቡ ጋር በሚኖረው ቀጣይነት ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ይጠበቃል። ጋርዲዮላ ዋንጫውን ለ3ኛ ጊዜ በማሸነፍ ከሚታወቁ አሰልጣኞች ተርታ ለመሰለፍ ያደረገው ፍልሚያም አልተሳካለትም፡፡
ባለፈው የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ዓመት የፈረንሳዩን ክለብ ፒኤስጂን እየመራ ለዋንጫ የቀረበው ቶማስ ቱሄል በባየር ሙኒክ ዋንጫውን መነጠቁ ይታወሳል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ከቼልሲ ጋር ለፍጻሜ ቀርቦ ፣ የሲቲ ተቀናቃኙን ጋርዲዮላን በመርታት ፣ ዋንጫውን አሳክቷል፡፡
ከፍተኛ የማሸነፍ ጉጉት የታየባቸው የቼልሲ ተጫዋቾች ጠንካራ ፍልሚያ ያደረጉ ሲሆን ፣ የመሀል ክፍሉን በብቃት ከመቆጣጠር ባለፈ ከመከላከል እስከማጥቃት ከፍተኛ ሚና የነበረው ንጎሎ ካንቴ የጨዋታው ኮከብ ሆኗል፡፡
በጋርዲዮላ ላይ የታክቲክ ብልጫ የያዘው ቱሄል በጥር ወር ቼልሲን መምራት ከጀመረ በኋላ ሲቲን በ3 ተከታታይ ጨዋታዎች ረትቷል፡፡