በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በአውሮፓ የሚካሔዱ የተለያዩ ውድድሮች እንዳይካሄዱ ውሳኔ ተላልፏል
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በአውሮፓ የሚካሔዱ የተለያዩ ውድድሮች እንዳይካሄዱ ውሳኔ ተላልፏል
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሁሉም የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ እና ዩሮፓ ሊግ ጨዋታዎች ሌላ ተጨማሪ መግለጫ እስኪወጣ ድረስ እንዲቋረጡ ተወሰነ፡፡
የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር 55 አባላት ዛሬ ባደረጉት ስብሰባ ለዩሮ 2020 የወንዶች እና ለ2021 የሴቶች ውድድር የሚደረጉ ማጣሪያዎች እና በሰኔ ወር ሊካሄዱ የታሰቡ የብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎችም እንዲቋረጡ መወሰኑን በድረ-ገጹ አስነብቧል፡፡
በአህጉሩ የወዳጅነትም ይሁን ማንኛውም ጨዋታ ማህበሩ ውሳኔውን እስኪቀለብስ ድረስ መካሄድ እንደማይችል ደንግገዋል፡፡
በቪዲዮ ኮንፈረንስ ውይይታቸውን ያደረጉት የአህጉሩ እግር ኳስ ገዢ አባላት ሁሉም የ2020/21 የክለቦች የውድድር ዓመት ማብቂያ ጊዜዎችም እንዲራዘሙ ወስነዋል፡፡ ይሁን እንጂ እስከመቼ የሚለው ጥያቄ በማህበሩ ቀጣይ ውሳኔ እንደሚታወቅ ነው የተገለጸው፡፡
በሌላ የስፖርት ዜና የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች እና ተጫዋቾቻቸው የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ድጋፍ እያደረጉ አይደለም በሚል እየተተቹ ነው፡፡
የብሪታኒያ ፖለቲከኞች የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች “የሞራል ክፍተት” አለባቸው ሲሉ ተችተዋቸዋል፡፡ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የክለቦቹ እና የተጫዋቾቻቸው ዝምታን መምረጥ የእንግሊዝ እግር ኳስ ምን ያክል የኢኮኖሚክስ ችግር እና የሞራል ቀውስ እንዳለበት ማሳያ ነው ሲሉ አንዳንዶች ትችታቸውን አቅርበዋል፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው የለንደን ከተማ ከንቲባ ሳዲቅ ክሀን “ተጫዋቾች በአሁኑ ወቅት ደሞዛቸውን መለገስ ይጠበቅባቸዋል” ያሉ ሲሆን በተለይ ከፍተኛ ተከፋይ ተጫዋቾች ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
የባርሴሎና ተጫዋቾች በሽታው በቁጥጥር ስር እስኪውል የደሞዛቸውን 70 በመቶ ለመለገስ ቃል የገቡ ሲሆን፣ የጁቬንቲዩስ ተጫዋቾች እና አሰልጣኙ ሞሪዚዮ ሳሪ ደግሞ የአራት ወር ደሞዛቸውን መለገሳቸው ይታወቃል፡፡
በጀርመን ደግሞ እንደ ባየር ሚዩኒክ እና ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ያሉ ክለቦችም ከደሞዛቸው ለመቁረጥ ተስማምተዋል፡፡