ሩሲያ ወታደራዊ የኬሚካል የጦር መሳሪያ እንደሌላት በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች
አሜሪካ ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ላይ ዓለም አቀፍ ስምምነትን በመጣስ የኬሚካል የጦር መሳሪያ ተጠቅማለች በማለት ከሳለች።
ሩሲያ በጦርነቱ ወቅት “ክሎሮፒክሪን” የተባለውን የኬሚካል የጦር መሳሪያ በዩክሬን ወታደሮች ላይ ተጠቅማለች በማለት ነው አሜሪካ የከሰሰችው።
ሩሲያ ተጠቅማዋለች የተባለው “ክሎሮፒክሪን” ኬሚካል ቀለም አለባ ፈሳሽ ሲሆን፤ በአይን፣ በቆዳ እና በጉሮሮ ላይ የማቃጠል ስሜት የሚፈጥር ነው ተብሏል።
ኬሚካሉ ከዚህ ቀደም በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በስፋት ጥቅም ላይወ ውሎ እንደነበረም አሜሪካ አስታውቃለች።
“ክሎሮፒክሪን” የተባለው የኬሚካል አሁን ላይ ፀረ ተባይ ሆኖ ጥቅም ላይ መዋሉን የቀጠለ ሲሆን፤ ከፈረንጆቹ 1993 ጀምሮ በጦር ሜዳ ጥቅም ላይ እንዳይውል እግድ ወጥቶበታል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴ ትናንት ባወጣው መግለጫ “እንዲህ ያሉ ኬሚካሎችን መጠቀም የተለየ ክስተት አይደለም” ያለ ሲሆን፤ ምናልባትም የዩክሬይን ኃይሎች ከመሸጉባቸው ቦታዎች ለማባረር እና በጦር ሜዳ ላይ የታክቲክ ጥቅሞችን ለማስገኘት ባላቸው ፍላጎት የተነሳ የተጠቀሙት ሊሆን ይችላል” ብሏል።
ሩሲያ ወታደራዊ የኬሚካል የጦር መሳሪያ እንደሌላት በተደጋጋሚ ስትገልጽ የቆየች ሲሆን፤ ነገር ግን ከመርዛማ ኬሚካሎች ጋር በተያያዘ ሀገሪቱ የበለጠ ግልፅነት እንዲኖራት ጫና እየተደረገባት ይገኛል።
ከክሎሮፒክሪን በተጨማሪ የሩሲያ ኃይሎች በሲኤስ እና በሲኤን ጋዝ የተጫኑ የእጅ ቦምቦችን ተጠቅመዋል ሲል የሮይተርስ የዩክሬን ጦርን ጠቅሶ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ መዘገቡ ይታወሳል።
ቢያንስ 500 የዩክሬን ወታደሮች ለመርዛማ ንጥረ ነገር በመጋለጣቸው ታክመው አንድ ሰው በአስለቃሽ ጭስ ታፍኖ መሞቱን ገልጿል።