አሜሪካ ለዩክሬን እስከ 300 ኪሎሜትር የሚምዘገዘጉ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን መላኳ ይታወሳል
ሩሲያ ስድስት አሜሪካ ሰራሽ ሚሳኤሎችን መትታ መጣሏን አስታወቀች።
ዩክሬን ባለፉት 24 ስአታት ባለስቲክ ሚሳኤሎች ወደ ክሬሚያ እና ሌሎች በሩሲያ በቁጥጥር ስር ወዳሉ አካባቢዎች መተኮሷ ተገልጿል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር “10 የዩክሬን ድሮኖች፣ ስድስት አሜሪካ ሰራሽ ታክቲካል ሚሳኤሎች እና ሁለት ከአውሮፕላን ላይ የሚተኮሱ “ሃመር” ቦምቦች በሩሲያ አየር መቃወሚያ ተመተዋል” የሚል መግለጫ አውጥቷል።
ሚኒስቴሩ ሚሳኤሎቹና ድሮኖቹ ተመተው የወደቁበትን ስፍራ ይፋ ባያደርግም የክሬሚያ አስተዳዳሪ ሰርጌ አክሲዮኖቭ፥ አሜሪካ ሰራሽ ባለስቲክ ሚሳኤሎቹ በክሬሚያ ልሳነ ምድር መውደቃቸውን ተናግረዋል።
ሩሲያ በተቆጣጠረቻቸው የደቡባዊ ዩክሬን ከተሞች ዛንኮይ እና ሲምፌሮፖል ከተሞችም የሩሲያ የአየር መቃወሚያዎች ሚሳኤሎችና ድሮኖችን መትተው መጣላቸው ነው የተገለጸው።
በክሬሚያ ተደጋጋሚ የጥቃት ሙከራዎችን ያደረገችው ኬቭ ከአሜሪካ የተላኩላት ሚሳኤሎች ተመተው ስለመውደቃቸው እስካሁን ያለችው ነገር የለም ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
አሜሪካ በቅርቡ 300 ኪሎሜትር የሚምዘገዘጉ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን ወደ ኬቭ በሚስጢር መላኳ መገለጹ ይታወሳል።
ረጅም ርቀት የሚጓዙት ሚሳኤሎች ወደ ሩሲያ ድንበር ዘልቀው በመግባት ጥቃት ሊያደርሱ ይችላሉ በሚል ስጋት ወደ ኬቭ ከመላክ ስታመነታ የቆየችው ዋሽንግተን በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትዕዛዝ ቁጥራቸው ያልተጠቀሰ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን ልካለች።
ይህም በጦር መሳሪያ እጥረት ምክንያት የተጓተተውን የኬቭ መልሶ ማጥቃት እንደሚያግዝ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ሞስኮ ግን የአሜሪካ ሚሳኤሎች “ዩክሬን ይበልጥ እንድትፈራርስ ከማድረግ ውጭ የሚያመጡት ለውጥ” የለም ማለቷ አይዘነጋም።