በከፍተኛ የአዕምሮ ህመም ስርጭት የተቸገረችው ቻይና የሶስት አመት ስትራቴጂ አዘጋጀች
እንደ የአለም ጤና ድርጅት መረጃ በሀገሪቱ 54 ሚሊየን በላይ ሰዎች የተለያዩ የአዕምሮ በሽታዎች ተጠቂ ናቸው
የበሽታው ስርጭት በታዳጊ እና በአዋቂ የእድሜ ክልል በሚገኙ ሰዎች ላይ መበርታቱ አስግቷል
የቻይና ብሔራዊ ጤና ኮሚሽን ከ2025 እስከ 2027 ባለው ጊዜ ውስጥ በአዕምሮ ጤና አገልግሎት ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለማስተካከል ስትራቴጂ ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡
የኮሚሽኑ ባለስልጣናት ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የአዕምሮ ጤና ዕክሎች በተለይም በታዳጊዎች እና በአዋቂ እድሜ ላይ በሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ እየተበራከቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሀገሪቱ የአዕምሮ ጤና መረጃዎችን የሚሰጡ የነጻ የስልክ መስመሮችን ለማዘጋጀት እንዲሁም በመላ ሀገሪቱ የአዕምሮ ጤና ማዕከላትን ለማቋቋም እና በአዕምሮ ጤና የሰለጠኑ የህክምና ባለሙያዎችን ለማሰማራት የጤና ኮሚሽኑ አቅዷል፡፡
በ 2025 በእያንዳንዱ ጠቅላይ ግዛት እና ከተማ ውስጥ የአዕምሮ እና የእንቅልፍ መዛባት ያለባቸው ተመላላሽ ታካሚዎችን የሚያገለግል ቢያንስ አንድ ሆስፒታል መኖር አለበት ተብሏል፡፡
በተጨማሪም በሶስት አመቱ ብሔራዊ የድርጊት መርሃ ግብር መሰረት ከ 95 በመቶ በላይ የሚሆኑት የቻይና ትምህርት ቤቶች በሙሉ ጊዜ ወይም በትርፍ ጊዜ የአዕምሮ ጤና ትምህርት እንዲማሩ ይደረጋል፡፡
በተጠናቀቀው 2024 ሁለት የመኪና ጥቃቶችን ጨምሮ ሌሎች አስከፊ ጥቃቶችን ባስተናገደችው ሀገር የዜጎች የአዕምሮ ጤና ጉዳይ ግንባር ቀደም ትኩረት የሚያሻው አጀንዳ ሆኗል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ከቻይና 1.4 ቢሊየን ህዝብ መካከል 54 ሚሊዮን ሰዎች በድብርት 41 ሚሊዮን ያህሉ ደግሞ በአዕምሮ ጭንቀት በሽታ እንደሚሳቃዩ ያመላክታል፡፡
የቻይና የዜና ወኪል ሽንዋ ባወጣው ዘገባ ደግሞ በጉርምስና እና በአዋቂ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች የመንፈስ ጭንቀት ወደ 2 በመቶ ገደማ እንደሚደርስ ጠቁሟል፡፡