ሶማሊያ የኢትዮጵያ ጦር በአዲሱ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ እንዳይሳተፍ ያሳለፈችውን ውሳኔ ለመቀየር እያጤነች እንደምትገኝ ተገለጸ
የኢትዮጵያ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ በዛሬው ዕለት ወደ ሞቃዲሾ ማምራታቸውን ብሉምበርግ ዘግቧል
ዘገባው ከአንካራው የመሪዎች ስምምነት በኋላ ሁለቱ ሀገራት በመካከላቸው ያለውን ውጥረት ለማርገብ ጥረት እያደረጉ ነው ብሏል
ሶማሊያ አትሚስን የሚተካው በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ (AUSSOM) ላይ የኢትዮጵያ ጦር እንዳይሳተፍ ያሳለፈችውን ውሳኔ ለመቀየር እያጤነች እንደምትገኝ ተነግሯል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ አዲስአበባ በተልዕኮው ስለምትሳተፍበት ጉዳይ ለመነጋገር ሀሙስ እለት ወደ ሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ መጓዛቸውን የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አሊ ባልካድ በስልክ ነግረውኛል ሲል ብሉምበርግ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ በጎረቤት ሶማሊያ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የአል ሸባብ ታጣቂዎችን ለመዋጋት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለሚደገፈው ሃይል ለአስርተ አመታት ዋነኛ አስተዋፅዖ ካደረጉ ሀገራት መካከል አንዷ ሆና ቆይታለች።
በባለፈው አመት ራስ ገዟ ሶማሊላንድ እና ኢትዮጵያ የተፈራረሙትን የወደብ የመግባብያ ስምምነት ተከትሎ ሁለቱ ጎረቤታም ሀገራት በዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ውስጥ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎም ሶማሊያ አዲስአበባ ከሀርጌሳ ጋር የገባችውን ስምምነት ካልሰረዘች በአዲሱ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ አትሳተፍም የሚል አቋም ስታንጸባርቅ ቆይታለች፡፡
በቅርቡ በቱርክ አደራዳሪነት ሀገራቱ በመሪዎቻቸው በኩል ግንኙነታቸውን ለማሻሻል ከስምምነት መድረሳቸውን ተከትሎ በመካከላቸው ያለውን ውጥረት ለማርገብ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
የዛሬው የኢትዮጵያ የመከላከያ ሚኒስትር የሞቃዲሾ ጉዞም ውጥረትን ለማርገብ እና የኢትዮጵን በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ተሳታፊነት ለማረጋገጥ የተደረገ መሆኑን ዘገባው አክሏል፡፡
የሶማሊያ ሚኒስትር ዴኤታ አሊ ባልካድ "በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል የነበሩ አከራካሪ ጉዳዮች በአንካራው ውይይት የተፈቱ በመሆናቸው ሶማሊያ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በመጪው (አውሶም) ተልዕኮ ውስጥ እንዲካተት ለማድረግ ውሳኔዋን በመመርመር ላይ ትገናለች" ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከሰላም ማስከበር ተልዕኮው መገለሏ በሁለቱ ሀገራት መካከል ግጭት ሊፈጥር እንደሚችል ዲፕሎማቶች ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል፡፡
አዲስ አበባ የአልሸባብ ታጣቂዎች ጥቃት ኢላማ ሆና የቆየች ሲሆን በተልዕኮው የረዥም ጊዜ ተሳትፎዋን ለማራዘም ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
በሌላ በኩል በአዲሱ ተልዕኮ የተካተተችው ግብጽ ሰራዊቶቿን በአየር እና በባህር ወደ ሶማሊያ ማስገባት መጀመሯን ዘ ናሽናል አስነብቧል፡፡