የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠ/ሚ ዐቢይ አዲሱን ዓመት በማይጠብሪ ግንባር ከሰራዊቱ ጋር እያከበሩ ነው
አዲሱ ዓመት “ለ30 ዓመታት ኢትዮጵያን የተጣባትን ፈተና” ተገላግለን “አዲስ መንግሥት የምንመሠርትበት” እንደሚሆን እምነቴ ነው ማለታቸው የሚታወስ ነው
ጠ/ሚ ዐቢይ በግንባሩ የሚገኘውን ሰራዊት ገለጻ ተደርጎላቸዋል
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ አዲሱን የ2014 ዓመት በማይጠብሪ ግንባር ከሰራዊቱ ጋር እያከበሩ ነው።
ጠቅላይ አዛዡ በግንባሩ ያለው ሠራዊት ቁመና እና የግዳጅ አፈፃፀም ብቃት አስመልክቶ በግንባሩ ከፍተኛ አመራሮች ገለፃ ተደርጎላቸዋል።
የሠራዊቱ አባላት ሕዝቡ ያሳያቸውን ከፍተኛ ድጋፍ የሞራል ስንቅ አድርገው ተልዕኳቸውን በላቀ ብቃት በመወጣት በአዲሱ ዓመት ለሕዝቡ ታላቅ የድል ብሥራት ለማሰማት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል እንደ ኢቢሲ ዘገባ።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ፣ ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሌተናል ጄነራል አበባው ታደሰ፣ የመከላከያ ኅብረት ዘመቻ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሜጄር ጄነራል ዘውዱ በላይ፣ የምእራብ እዝ እና የማይጠብሪ ግንባር አዛዥ ሜጄር ጄነራል መሠለ መሠረትን ጨምሮ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች በዓሉን ከሠራዊቱ ጋር ለማክበር በስፍራው ተገኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አዲሱን ዓመት አስመልክተው ትናንት ባስተላለፉት መልዕክት አዲሱ ዓመት “ለ30 ዓመታት ኢትዮጵያን የተጣባትን ፈተና” ተገላግለን “አዲስ መንግሥት የምንመሠርትበት እንደሚሆን እምነቴ ነው” ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ወደ አዲሱ ዘመን የምናደርገው ሽግግር የሚጎዱንን አሮጌ ማንነቶች በመጣልና በአዲስ ጠቃሚ ማንነቶች በመተካት መሆን አለበት” ማለታቸውም አይዘነጋም።
ኢትዮጵያውያን አዲሱን ዓመት በተለያዩ ስነ ስርዓቶች እያከበሩ ነው።