በአሜሪካ በህገወጥ ስደተኛ መጠለያ ጣብያዎች ውስጥ ህጻናት ጾታዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው ተገለጸ
ጥቃቱ የተፈጸመው ባለፉት ስምንት አመታት መጠለያዎቹ በሚገኙባቸው ሶስት ግዛቶች ነው ተብሏል
ህጻናቱ አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ ስድስት አይነት ጾታዊ ጥቃት ይደርስባቸው ነበር
በአሜሪካ በህገወጥ ስደተኛ መጠለያ ጣብያዎች ውስጥ ህጻናት ጾታዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው ተገለጸ።
ከላቲን አሜሪካ ሀገራት ብቻቸውን በሚሰደዱ ህገ ወጥ ስደተኛ ህጻናት ማቆያዎች ውስጥ ጾታዊ ጥቃት እንደሚደርስ የአሜሪካ ፍትህ ሚንስቴር አስታወቀ፡፡
ባለፉት ስምንት አመታት ሳውዝ ዌስት ኪይ በተባለ ለትርፍ ባልተቋቋመ ድርጅት ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች በህጻናቱ ላይ አስገድዶ መድፈር፣ አካላዊ ጉንተላ፣ እርቃን ፎቶ ማንሳትን ጨምሮ በአጠቃላይ ስድስት አይነት የጾታዊ ጥቃቶችን ያደርሱ እንደነበር የፍትህ ሚንስቴሩ በከፈተው የክስ መዝገብ ላይ አመላክቷል፡፡
በአሪዞና ፣ ቴክሳስ እና ካሊፎርኒያ በሚገኙ 29 የህጻናት ማቆያዎች ውስጥ ከ2015 እስከ 2023 ወንጀሉ ተፈጽሟል የተባለ ሲሆን ፤ ሳውዝ ዌስት ኪይ የተባለው ድርጅት ለህጻናቱ መጠለያዎችን ማስተዳደር እና አስፈላጊውን አገልግሎት ለመስጠት ከአሜሪካ መንግስት ኮንትራት ገብቶ ሲሰራ የነበረ ድርጅት ነው ተብሏል፡፡
ድርጅቱ በእነዚህ አመታት 3 ቢሊየን ዶላር ከአሜሪካ መንግስት አግኝቷል።
ጥቃቱ የሚደርስባቸው ህጻናት ጉዳዩን ሪፖርት የሚያደርጉ ከሆነ የምግብ እና ሌሎች አገልግሎቶችን እንደማያገኙ እና ከመጠለያው እንደሚባረሩ በጥቃት አድራሾቹ ማስፈራርያ እና ዛቻ እንደሚደርስባቸውም ተሰምቷል፡፡
በጉዳዩ ላይ ከ2018 ጀምሮ ጥቆማዎች ይቀርቡለት እንደነበር ያስታወቀው የፍትህ ቢሮው ድርጅቱ በጉዳዩ ላይ ምርመራ እና ማስተካከያዎቹን እንዲያደርግ በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ቢሰጥም ጥቃቱ አሁንም ቀጥሏል ሲል ከሷል፡፡
በጥቃቱ ምን ያህል ህጻናት ሰለባ እንደሆኑ ይፋዊ የቁጥር መረጃዎች ባይወጡም 6300 ህጻናትን ማስተናገድ የሚችሉ 29 ተቋማት እንዳሉት በተነገረው ተቋም በአጠቃላይ 100 ጥቆማዎች እንደቀረቡ ነው የተነገረው፡፡
ፕሬዝዳንት ጆባይደን ስልጣን ከያዙ ጀምሮ በአሜሪካ ደቡባዊ ድንበር ላይ ህገ ወጥ ስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ የጨመረ ሲሆን ከ2021 ጀምሮ 8.2 ሚሊየን ስደተኞች በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ለማቋረጥ ሙከራ ማድረጋቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በባራክ ኦባማ በሁለቱም የስልጣን ዘመን እና በዶናልድ ትራምፕ ዘመን የህገ ወጥ ስደተኞች ቁጥር በአንድ ላይ ተደምሮ ከ5.5 ሚሊየን አይሻገርም፡፡
ድርጅቱ በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ መሆኑ ከተረጋገጠ ኮንትራቱ ተሰርዞ ድርጅቱ እስከመዘጋት እና በጥፋተኞቹ ላይ የእስር ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ኤፒ ዘግቧል፡፡