ከአውሮፓ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ በፊት የእንግሊዝን አሸናፊነት የሚገልጽ ንቅሳት የተነቀሰው እንግሊዛዊ
እንግሊዝ ዋንጫውን ብትሸነፍም በንቅሳቱ አልጸጸትም ያለው ግለሰቡ ሌሎችም ለብሔራዊ ቡድኑ ድጋፍቸውን ድገፍ ለመግለጽ ተመሳሳዩን እንዲያደርጉ ጠይቋል
ትላንት በተደረገው የአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ ጨዋታ ስፔን እንግሊዝን 2ለ1 አሸንፋ ዋንጫውን አንስታለች
በዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ እንግሊዝ እንደምታሸነፍ የሚገልጽ ንቅሳት የተነቀሰው እንግሊዛዊ በውሳኔዬ አልጸጸትም ብሏል፡፡
ዳን ቶማስ የተባለው የ29 አመት እንግሊዛዊ “የ2024 አውሮፓ ዋንጫ አሸናፊ እንግሊዝ" የሚል ንቅሳት በግራ እግሩ ላይ ከጨዋታው አንድ ቀን በፊት ተነቅሷል፡፡
ምሽት በተካሄደው ጨዋታ ለ60 አመታት ከዋንጫ ውጭ ሆኖ የቆው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ድል ባይቀናውም ደጋፊው ቡድኑ እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ ነበርኩ ብሏል፡፡
ግለሰቡ የእንግሊዝን አሸናፊነት ከሚገልጸው ጽሁፍ ባለፈ የውድድሩን ዋንጫ በግራ እግሩ ላይ የተነቀሰ ሲሆን ሁለት ሰአት ተኩል የፈጀውን የንቅሳቱን ሂደት በቲክቶክ ባስተላለፈበት ወቅት ከ42ሺ በላይ ተመልካቾች እንደነበሩት ደይሊ ሜል አስነብቧል፡፡
ቶማስ “ለዋንጫው በጣም ተቃራበን ነበር ቡድኑ የሚችለውን ሁሉ እንዳደረገ ይሰማኛል። ምንም እንኳን ዋንጫውን ባናሸንፍም የብሔራዊ ቡድኑ ደጋፊዎች ለሶስቱ አናብስት ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ እንደ እኔ ንቅሳት እንዲነቀሱ እመክራለሁ” ብሏል፡፡
የቡድኑን ሽንፈት ተከትሎ ወዳጆቹ ንቅሳቱን እንዲያስጠፋው እየመከሩት እንደሚገኙ የገለጸው ቶማስ “አራት ቁጥርን ወደ ስምንት መቀየር ብዙ አያስቸግርም በ2028 በሚደረገው የአውሮፓ ዋንጫ እንግሊዝ ስለምታሸነፍ በዚህ ጊዜ ንቅሳቴን አስተካክለዋለሁ፤ እስከዛው ድረስ ግን የማፍረበት ነገር አይደለም” ነው ያለው፡፡
ንቅሳቱን የነቀሰው የንቅሳት ባለሙያ “ቶማስ ከጨዋታው በፊት እንግሊዝ ማሸነፏን የሚገልጽ ንቅሳት እንድነቅሰው ሲጠይቀኝ ደጋግሞ እንዲያስብበት እና ጨዋታው ከተደረገ በኋላ እንዲመለስ ብጠይቀውም በቡድኑ ያለኝን እምነት ለማሳየት ከጨዋታው በፊት ማድረግ ነው የምፈልገው በሚል አቋሙ ስለጸና” ንቅሳቱን ሊነቅሰው እንደቻለ ተናግሯል፡፡
በ2024 የአውሮፓ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ እንግሊዝን ያሸነፈችው ስፔን የውድድሩ ሻምፒዮን ስትሆን በተጨማሪም የአውሮፓ ዋንጫን አራት ጊዜ በማንሳት የመጀመሪያ ሀገር መሆን ችላለች፡፡
የስፔን ብሔራዊ ቡድን የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንን 2ለ1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ነው የ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ሻምፒዮን የሆነው።
ለስፔን ብሔራዊ ቡድን የማሸነፊያ ግቦችን ኒኮ ዊሊያምስ እና ሚኬል ኦያርዛባል ከመረብ ሲያሳርፉ፤ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንን ከሽንፈት ያልታደገች ግብ ኮል ፓልመር ማስቆጠር ችሏል።