አሜሪካውያን በኮንጎው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተገደው መሳተፋቸውን ተናገሩ
የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገውን ኮንጓዊ የመፈንቅለ መንግስት መሪ ክርስቲያን ማላንጋን ገድለዋል
ተከሰው ፍርድ ቤት የቀረቡት ሁለት አሜሪካውያን በመፈንቅለ መንግስት መሪው እንዲሳተፉ መገደዳቸውን ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል
አሜሪካውያን በኮንጎው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተገደው መሳተፋቸውን ተናገሩ።
በዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተካሄደው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በነበራቸው ሚና ምክንያት ተከሰው ፍርድ ቤት የቀረቡት ሁለት አሜሪካውያን በመፈንቅለ መንግስት መሪው እንዲሳተፉ መገደዳቸውን ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።
በፈረንጆቹ ባለፈው ግንቦት 19 በተካሄደው በዚህ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ወቅት፣ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገውን ኮንጓዊ የመፈንቅለ መንግስት መሪ ክርስቲያን ማላንጋን ገድለዋል።
የክስ ሂደቱ ከተጀመረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተናገረው የ22 አመቱ ማላንጋ ልጅ ማርሴል ማላንጋ እና ቤንጃሚን ዛልማን ፖሉን ለፍርድ ቤቱ እንደተናገሩት የመፈንቅለ መንግስት መሪው አስፈራርቷቸው ነበር።
"አባቴ ትዕዛዙን ካልተቀበልን እንደሚገድለን አስፈራርቶናል" ሲል ለወታደራዊ ፍርድ ቤቱ የተናገረው ማርሴል ማላንጋ በሴራው ላይ እንደሌለበት አስተባብሏል።
ልጁ ወደ ኮንጎ የመጣው ከፈረንጆቹ 2021 ጀምሮ ያላየውን አባቱን ለማየት በእሱ ግብዣ መምጣቱን ገልጿል።"እኔ አሜሪካዊ ነኝ፤ ፈረንሳይኛም ሆነ ሊንጋላ አልችልም"።
ሁለቱ ግለሰቦች፣ በህገወጥ መንገድ የጦር መሳሪያ ይዞ በመገኘት፣ በማሴር፣ በሽብር፣ የሀገር ተቋማትን አለመረጋጋት ውስጥ በመክተት እና የሀገሪቱ ደህንነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ክስ የቀረበባቸው ሲሆን የሞት ፍርድ ወይም የረጅም ጊዜ እስራት ሊፈረድባቸው ይችላል ተብሏል።
ዛልማን ፖሉን የመላንጋ የረጅም ጊዜ የቢዝነስ አጋር መሆኑን እና መፈንቅለ መንግሰት በማቀድ እጁ እንደሌለበት ተናግሯል።
"ማላንጋን ያገኘሁት በፈረንጆቹ 2013 ነበር፤ ሁል ጊዜ የምናወራውም በስዋዚላንድ እና በሞዛምቢክ ልናደርግ ስለምንችልው የማዕድን ማውጣት ጉዳይ ነበር፣ አመጸኛ አልነበረም" ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል።