በአፍሪካ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ አሸባሪዎች አቅም እያደገ መሆኑ ተነገረ
በአህጉሪቱ የሚንቀሳቀሱ አሸባሪዎች በአሜሪካ እና ምእራባዊያን ሀገራት ላይ ጥቃት እንዳይሰነዝሩ ተሰግቷል
ከሳህል ቀጠና ወታደሮቿን በማስወጣት ላይ የምትገኝው አሜሪካ በአካባቢው ወታደራዊ አጋር ፍለጋ ላይ ትገኛለች
አልቃይዳ እና አይኤስ ጋር ግንኙነት አላቸው የሚባሉ በአፍሪካ የሚገኙ ጽንፈኛ አሸባሪዎች አቅም እየጨመረ እንደሚገኝ ተነገረ፡፡
አሸባሪዎቹ በአህጉሪቷ በተለያዩ ስፍራዎች ላይ ያላቸው ተጽእኖ እየጨመረ እንደሚገኝ ያስታወቀችው አሜሪካ ሁሉን አቀፍ መፍትሄ ያስፈልጋል ብላለች፡፡
አፍሪካ ከመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ቀጥሎ የጽንፈኛ ሽብርተኞች መፈልፈያ እና መገኛ ሆናለች የሚለው የአሜሪካ የደህንነት መስሪያ ቤቶች መረጃ ሽብርተኞቹ በምዕራባዊያን ሀገራት እና በአሜሪካ ጥቃት ሊፈጽሙ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል፡፡
የአፍሪካ አሜሪካ ወታደራዊ አጋርነት ጉባኤ በቦትስዋና እየተካሄደ ይገኛል ፡፡ በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የአሜሪካ አየር ሀይል አዛዥ ጄነራል ቻርልስ ብራውን በተለይም በሳህል ቀጠና የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች በተጽእኖ እና በታጣቂዎች ቁጥር አቅማቸው እያደገ ነው ብለዋል፡፡
አይኤስ ፣ አልሸባብ እንዲሁም በማሊ ቡርኪናፋሶ እና ኒጄር የሚንቀሳቀሰው “ጄኤንአይኤም” የተሰኝው ታጣቂ በጋራ እየሰሩ እንደሚገኝ መረጃዎችን መጠቆማቸውን ያነሱት ጄነራሉ ሌሎች በሳህል ቀጠና እና በምእራብ አፍሪካ የሚገኙ ታጣቂዎችም በጋራ ለመስራት እየተስማሙ ስለመሆናቸው አስጠንቅቀዋል፡፡
በውግያ ታክቲክ እና የዘመቻ ልምድ አካብተዋል ያሏቸው ታጣቂዎች ከአፍሪካ ተሻግረው በምዕራቡ አለም ጥቃት የመፈጸም ጉልበት ሳይገነቡ አይቀርም ነው ያሉት፡፡
በሳህል ቀጠና ያልተረጋጋው ፖለቲካዊ ሁኔታ ለሽብርተኞቹ መፈርጠም አድል ፈጥሯል ያሉት ጀነራሉ ይህን ለመከላከል ዋሽንግተን በአካባቢው ካሉ ሀገራት ጋር ለመስራት ዝግጁ ናት ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በ4 አመታት ውስጥ 6 መፈንቅለ መንግስቶችን ያስተናገደው የምዕራብ አፍሪካ ቀጠና በወታደራዊ አመራሮች እየተመራ ይገኛል፡፡
በዚህ አካባቢ ወታደሮቿን አሰማርታ የሽብረተኞች እንቅስቃሴን ስትቃኝ የቆየችው አሜሪካ ኒጄር እና ቻድን ጨምሮ ከሌሎች የሳህል ቀጠና ሀገራት ጦሯን እያስወጣች ትገኛለች፡፡
ሀገሪቱ እስከ መስከረም ድረስ በኒጄር የሚገኙ አንድ ሺህ ወታደሮቿን ሙሉ ለሙሉ ለማስወጣት አቅዳለች፡፡
በቀጠናው አዲስ የተመሰረቱት ወታደራዊ መንግስታት ከአሜሪካ ይልቅ የሩሲያን አጋርነት መርጠዋል በዚህ የተነሳም በሀገራቸው የሚገኝው የአሜሪካ ጦር ለቆ እንዲወጣ እየጠየቁ ይገኛሉ፡፡
ይህን ተከትሎም በቀጠናው የሚንቀሳቀሱ ሽብርተኞችን በቅርበት ለመከታተል እና እርምጃዎችን ለመውሰድ በአካባቢው የጦሩ መቆየት የሚያስፈልጋት ዋሽንግተን ከሌሎች የአካባቢው ሀገራት ጋር በወታደራዊ አጋርነት ዙርያ ድርድር ጀምራለች፡፡
የአሜሪካ የመከላከያ መስርያቤት ፔንታጎን ማረጋገጫ ባይሰጥም ኤፒ ሮይተርስን ጠቅሶ እንደዘገበው የኒጄር ጎረቤቶች የሆኑት አይቮሪኮስት ፣ ቤኒን እና ጋና ቀጣዮቹ የአሜሪካ ጦር ማረፊያ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስነብቧል፡፡