የቻይና ህዝብ ቁጥር ለሁለተኛ ተከታታይ አመት ቀነሰ
በእስያዊቷ ሀገር በ2023 9 ሚሊየን ህጻናት ተወልደው 11 ነጥብ 1 ሚሊየን ሰዎች ህይወታቸው አልፏል
ህንድ ባለፈው አመት ቻይናን በመብለጥ የአለማችን ባለብዙ ህዝብ ሀገር መሆኗ ይታወሳል
የቻይና ህዝብ ቁጥር ለሁለተኛ ተከታታይ አመት መቀነሱ ተነገረ።
የሀገሪቱ የስታስቲክስ ቢሮ እንዳስታወቀው በ2023 የቻይና የህዝብ ቁጥር በ2 ነጥብ 08 ሚሊየን ቀንሷል።
ይህም በ2022 ከተመዘገበው የ850 ሺህ ህዝብ ቁጥር ቅናሽ ከእጥፍ በላይ መሆኑ ተገልጿል።
ቤጂንግ በ2022 ያጋጠማት የህዝብ ቁጥር መቀነስ በፈረንጆቹ 1961 በማኦ ዜዶንግ የስልጣን ዘመን የተከሰተው ከባድ የረሃብ አደጋ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ያጋጠመ እንደነበር ይታወሳል።
የቻይና ስታስቲክስ ቢሮ መረጃ እንደሚያሳየው በ2023 የውልደት ምጣኔው ወደ 5 ነጥብ 7 በመቶ ዝቅ ብሎ 9 ነጥብ 02 ሚሊየን ህጻናት ተወልደዋል፤ ከ1 ሺህ ሰው 6 ነጥብ 39 ሰዎች ይወለዳሉ እንደማለት።
በአንጻሩ የሞት ምጣኔው ወደ 6 ነጥብ 6 በመቶ አድጎ 11 ነጥብ 1 ሚሊየን ሰዎች ህይወታቸው ማለቱ ነው የተጠቀሰው።
በ2023 የተመዘገበው የሞት መጠን ከ1974ቱ የባህል አቢዮት በኋላ ከፍተኛው መሆኑም ተጠቁሟል።
የኮሮና ወረርሽኝ በጠቅላላ ኢኮኖሚው ውስጥ ያስከተለው ተጽዕኖና የወጣቶች የስራ እድል እየተመናመነ መሄድ የቻይናን የህዝብ ቁጥር እየቀነሰ እንዲሄድ ማድረጉን ሬውተርስ ዘግቧል።
ቤጂንግ ከ1980 እስከ 2015 የተገበረችው የአንድ ህጻን ፖሊሲ ግን ዋነኛው የህዝብ እድገቱ ማነቆ መሆኑ ተደጋግሞ ይነሳል።
የአለማችን ሁለተኛዋ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ሀገር እድሜያቸው ከ60 በላይ የሆኑ ዜጎቿ ቁጥር እየጨመረ ነው፤ በ2023 በ21 ነጥብ 1 በመቶ አድጎ 296 ነጥብ 97 ሚሊየን ደርሷል።
በ2050 የቻይና ህዝብ ቁጥር በ109 ሚሊየን እንደሚቀንስ የመንግስታቱ ድርጅት ትንበያ ያሳያል።
ይህም በ2019 ከነበረው ትንበያ በሶስት እጥፍ መጨመሩን የሚያነሱ የድርጅቱ ባለሙያዎች የህዝብ ቁጥር መቀነስ በቤጂንግ ኢኮኖሚ ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተጽዕኖ ቀላል አይሆንም ብለዋል።
የቻይናን ህዝብ ብዛት መሰረት አድርገው ቢዝነሳቸውን የጀመሩ ኩባንያዎችም ባለፈው አመት ቤጂንግን በመብለጥ ቀዳሚዋ የአለማችን ባለብዙ ሀገር ወደሆነችው ህንድ ፊታቸውን ሊያዞሩ እንደሚችሉ እያሳሰቡ ነው።