የአንድ ሰው የጠፈር የጉዞ ትኬት ዋጋም ከ287 ሺህ እስከ 430 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ይሆናል ተብሏል
ቻይና በፈረንጆቹ 2025 የግል ተጓዦችን በክፍያ ወደ ጠፈር ለማጓጓዘ እየሰራች መሆኑ ተገለፀ።
አንድ የቻይና የሮኬት ተመራማሪ እንዳስታወቁት ከሆነ የአንድ ሰው የጉዞ ዋጋ 2 እና 3 ሚሊየን የቻይና ዩዋን (ከ287 ሺህ እስከ 430 ሺህ የአሜሪካ ዶላር) ሊሆን እንደሚችል አስታውቀዋል።
በፈረንጆቹ በ2018 የተመሰረተው የሎንግ ማርች ሮክት ዋና ዳይሬክተር እና መቀመጫውን ቤጂንግ ያደረገው ሲ.ኤ.ኤስ ስፔስ ኤጀንሲ መስራች የሆኑት የሮክት ተመራማሪው ያንግ ዪክያንግ፤ ግለሰቦችን ወደ ጠፈር ለማጓጓ ሶስት አይነት የመጓጓዣ ዘዴዎች መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
የመጀመሪያው ወደ ዓለም አቀፍ የጠፈር ማዕከል መግባት የሚያስችል ሲሆን፤ ይህም ለቱሪስቶች ጥብቅ የሆነ የአካላዊ እና የስነ ልቦናዊ ቅድመ ሁኔታዎችን የሚያሰቀምጥ ነው ተብሏል።
ሁለተኛው የጉዞ አይነት ቱሪስቶች መንኮራኩር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ በሌላ በካርጎ መንኮራኩር ወደ ጠፈር እንዲሄዱ ማድረግ የሚያስችል ሲሆን፤ ይህኛው ጉዞ በአንድ መቀመጫ 450 ሺህ ዶላር እንደሚያስከፍል ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
ሶስተኛው የጉዞ አይነት ሰብ ኦርቢታል የሚባል ሲሆን፤ ይህኛው የጉዞ አይነት ለአብዛኞቹ ጎብኚዎች የተመቸ እንደመሆን የሮክት ተመራማሪው ያንግ ዪክያንግ ገልፀዋል።