ታይዋን በዛሬው እለት ባወጣችው መግለጫ፥ በደሴቷ አቅራቢያ የተደረገውን ወታደራዊ ልምምድ አውግዛለች
ቻይና በትናትናው እለት በታይዋን የጦር ልምምድ ማድረጓን አስታወቀች።
የሀገሪቱ የምስራቅ እዝ እንዳስታወቀው፥ በታይዋን አቅራቢያ በተደረገው ወታደራዊ ልምምድ 28 አውሮፕላኖች ተሳትፈዋል።
በባህርና በአየር ሊቃጡ የሚችሉ ጥቃቶችን መመከትና መሰንዘር የሚያስችል ልምሜድ መደረጉንም እዙ ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
- ቻይና በታይዋን ዙሪያ ባደረገቸው ወታደራዊ ልምምድ 71 የጦር አውሮፕላኖችን ማሰማራቷ ተገለጸ
- አሜሪካ ለታይዋን 180 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎችን ለመሸጥ ተስማማች
የቤጂንግ አውሮፕላኖች በወር ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ያደረጉት ወታደራዊ ልምምድ የቤጂንግ እና ታየፒን ፍጥጫ አንሮታል።
ታይዋን በዛሬው እለት ባወጣችው መግለጫ፥ ቻይና በደሴቷ አቅራቢያ ያደረገችውን ወታደራዊ ልምምድ አውግዛለች።
በታይዋን ሰርጥ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ጉዳይ የቤጂንግም ሆነ የታይፒ የጋራ ሃላፊነት መሆኑንም ነው ያስታወቀችው።
ደሴቷ ውጥረቱን ማባባስ እንደማትፈልግ የገለፀች ሲሆን፥ ሉአለዊነቴንና ደህንነቴን ለማረጋገጥ ግን ወደኋላ አልልም ማለቷን ሬውተርስ ዘግቧል።
ቻይና ግን ደሴቷ የሉአላዊ ግዛቴ አንድ አካል ናት ብላ በፅኑ ታምናለች።
የቀድሞ የአሜሪካ የህዝብ ተወካዬች ምክርቤት አፈጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ፥ ባለፈው አመት ታይዋንን ከጎበኙ በኋላ ውጥረቱ ተባብሷል።
ዋሽንግተን ለታይፒ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ለመሸጥ የገባችው ስምምነትም ቤጂንግን አስቆጥቷል።
በዩክሬን ሩሲያን እየገጠመች ያለችው አሜሪካ፥ በታይዋን ሌላኛዋን ተገዳዳሪ ልዕለ ሃያል ቻይና በእጅ አዙር ለመፋለም እየተሰናዳች ነው የሚሉ ወቀሳዎች ከቤጂንግ ይደመጣል።
ዋይተሃውስ ግን ውንጀላውን እንደማትቀበለው በተደጋጋሚ እየገለፀች፥ የጦር መሳሪያ ማስታጠቁን ገፍታበታለች።