
ከቻይና በተጨማሪም አውሮፓውያንም የመከላከያ በጀታቸውን እየጨመሩ ናቸው
ቻይና ለመከላከያ ዓመታዊ በጀቷ 245 ቢሊዮን ዶላር መደበች፡፡
የዓለማችን ቁጥር ሁለት ሀያል ሀገር የሆነችው ቻይና በዓመታዊ በጀቷ ላይ ጭማሪ አድርጋለች፡፡
ሀገሪቱ በቅርቡ ለተቀበለችው የ2025 አዲስ ዓመት 1 ነጥብ 8 ትሪሊዮን ዩዋን ወይም 245 ቢሊዮን ዶላር መመደቧ ተገልጿል፡፡
የበጀት መጠኑ ካለፈው የ2024 ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ7 ነጥብ 2 በመቶ ጭማሪ አሰይቷል፡፡
የቻይና ዓመታዊ የመከላከያ በጀት ከተቀናቃኟ አሜሪካ ጋር ሲነጻጸር በሶስት እጥፍ ያነሰ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ቻይና ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ ለመከላከያ የምትመድበው ዓመታዊ በጀት በየጊዜው እየጨመረ የመጣ ሲሆን በተለይም የበጀት ጭማሪው ከኢኮኖሚ እድገቱ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
የዓለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ የሚባሉ ሀገራት ለመከላከያ እየመደቡት ያለው በጀት በየጊዜው እየጨመረ የመጣ ሲሆን ከአሜሪካ እና ቻይና በተጨማሪ አውሮፓዊያንም እየጨመሩ ይገኛሉ፡፡
በተለይም ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬን ጦርነት እንዲቆም ግፊት ማድረግ ከጀመሩ በኋላ አውሮፓዊን ሀገራት በደህንነት ስጋት ምክንያት በጀታቸውን ለመጨመር ተስማምተዋ፡፡
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የአባል ሀገራቱን መከላከያ አቅም ለማሳደግ የ800 ቢሊዮን ዩሮ እቅድ በትናትናው ዕለት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡