ቻይና በዓለማችን ውድ የሚባለውን አዲስ ማዕድን አገኘች
ማዕድኑ ቻይናዊንን እድሜ ልክ መብራት እንዲያገኙ የሚያደርግ ሲሆን አንድ ሚሊዮን ቶን መጠን ያለው ቶሪየም ማዕድን ተገኝቷል

ቶሪየም የሚባለው ማዕድን ከሀይል ማመንጨት ባለፈ እንደ ካሜራ፣ ሴራሚክስ፣ የቴሌስኮፕ ሌንስ እና መሰል ምርቶችን ለማምረት ጥቅም ላይ ይውላል
ቻይና በዓለማችን ውድ የሚባለውን አዲስ ማዕድን አገኘች፡፡
የዓለማችን ሁለተኛዋ ልዕለ ሀያል ሀገር የሆነችው ቻይና ቶሪየም የተሰኘውን ተፈላጊ ማዕድን ማግኘቷን አረጋግጣለች፡፡
ሀገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር በሚል የዲፕሎማሲ እና የፊት ለፊት ግጭት ውስጥ ሲገቡ የሚታይ ሲሆን ከነዚህ ምክንያቶች መካከል አንዱ የሀይል ፍላጎትን ለማረጋገጥ ሀብት ፍለጋ ዋነኛው ነው፡፡
ነዳጅ ለረጅም ዓመታት ዋነኛ የሀይል ምንጭ መሆኑን ተከትሎ ሀገራት ፍላጎታቸውን ለማስከበር የተለያዩ ጥረቶችን ሲከተሉ ቆይተዋል፡፡
አሁን ላይ የዓለም የሀይል ምንጭ ወደ ታዳሽ እና የከፋ የአካባቢ ብክለት የማያደርስ አማራጭ በመፈለግ ላይ ሲሆን የጸሀይ ሀይል፣ ከውሃ የሚመነጭ የሀይል አማራጭ እና የኑክሌር ሀይል ዋነኛ አማራጮች ናቸው፡፡
ዩራኒየም እና ቶሪየም ደግሞ ለኑክሌር ሀይል አማራጭ ዋነኛ ግብዓት ሲሆኑ ዩራኒየም ማዕድን እንደ ልብ አለመገኘት፣ ማዕድኑም በተወሰኑ የዓለማችን ሀገራት ብቻ መገኘቱ እጥረቱን ሲያባብሰው ቆይቷል፡፡
ቻይና አገኘሁት ያለችው ቶሪየም ማዕድን አንድ ሚሊዮን ቶን መጠን አለው የተባለ ሲሆን ሀገሪቱ የሀይል ፍላጎቷን ለ60 ሺህ ዓመታት እንድትሸፍን ይጠቅማታል ተብሏል፡፡
እንደ መንግስታዊው የሳውዝ ቻይና ፖስት ዘገባ ከሆነ ቶሪየም ማዕድኑ የተገኘው በደቡባዊ የሀገሪቱ አካባቢ ሞንጎሊያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡
ቶሪየም ማዕድን በተለይም የኑክሌር ሀይልን ለማመንጨት፣ ቴሌስኮፕ ሌንሶችን፣ ሴራሚክ፣ ካሜራዎችን እና ሌሎች ተፈላጊ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን ለማምረት ይውላል፡፡
የማዕድኑ መገኘት ቻይና በኑክሌር ሀይል እና ተያያዥ ቴክኖሎጂ ዘርፍ የዓለም መሪ ለመሆን ለያዘችው እቅድ ትልቅ ግብዓት ይሆናታል ተብሏል፡፡
ቶሪየም ማዕድን ከዩራኒየም ጋር ሲነጻጸር በቀላሉ ሀይል እንዲፈጠር በማድረግ እና በአካባቢ ላይ የሚያደርሰው ብክለት ዝቅተኛ መሆኑ የወደፊቱ ተመራጭ የሀይል ግብዓት እንደሚሆን በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡